ሉሲን ጨምሮ ለሰው ልጆች ዝግመተ ለውጥ መነሻ የሆነውን “ሃዳር” ያገኙት ተመራማሪ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
የስነ-ምድር ተመራማሪው ዶክተር ሞውራይስ በ86 ዓመታችው ነው ህይወታቸው ያለፈው
ዶ/ር ሞውራይስ ታይብ ሃዳር ለሰው ልጆች ዝግመተ ለውጥ መነሻ መሆኑን በፈረንጆቹ 1968 ላይ ነበር የጠቆሙት
ለሉሲ ቅሪተ አካል መገኘት እና ለሰው ልጆች ዝግመተ ለውጥ መነሻ የሆነውን “ሃዳር” የተሰኘ ስፋራ ያገኙት የስነ-ምድር ተመራማሪ ዶ/ር ሞውራይስ ታይብ ከዚህች ዓለም በሞት ተለዩ።
የስነ-ምድር ተመራማሪው ዶክተር ሞውራይስ በ86 ዓመታችው ህይወታቸው ማፉን የፈረንሳዩ ብሔራዊ የሳይንስ ምርምር ማዕከል አስታውቋል።
ዶክተር ሞውራይስ ታይብ በአፋር ክልል የሚገኘው እና “ሃዳር” የተባለው ስፍራ በርካታ ጥንተ-ቅሪተ አካል ሊገኝበት እንደሚችል ቀደም ብለው ምርምር ካደረጉ ተመራማሪዎች መካካል አንዱ እንደነበሩም ማዕከሉ ገልጿል።
ተመራማሪው የ3.2 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ባለቤት የሆነችው የአውስትራሎ ፒተከስ አፋረንሲስ በልዩ መጠሪያ ስሟ “ሉሲ” ቅሪተ አካል በስነ-ምህዳር ምርምር መገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው።
ሉሲ የተገኘችው እ.ኤ.አ 1974 ሲሆን፤ ዶ/ር ሞውራይስ ታይብ ከባለደረቦቻቸው ጋር በመሆን የሃዳር ስፍራን የሰው ልጆች መነሻ መሆኑን የጠቆሙት 1968 ላይ ነበር።
ዶክተር ሞውራይስ ታይብ እኤአ በ1935 በቱኒዚያ የተወለዱ ሲሆን፤ የዶክትሬት ትምህረታቸውን የእናታቸው ትውልድ ሀገር ወደ ሆነችው ሆነችው ፈረንሳይ በመጓዝ ተከታትለዋል፤ እ.ኤ.አ በ1974 ከፓሪስ VI ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዲግሪያቸው አግኝተዋል።
ተመራማሪው እ.ኤ.አ በ1972 በአፋር አካባቢ የቅሪተ አካል ምርምር ማድረግ የሚያስችላቸውን ዓለም አቀፍ የአፋር የምርምር ማዕከል /International Afar Research Expedition (IARE)/ን በማቋቋም ከሁለት ዓመታት በኋላ ከምርምር ባልደረቦቻቸው ዶናልድ ጆሃንሰን እና ይቨስ ኮፐንስ ጋር በመሆን በዓለም በሰው ዝግመተ-ለውጥ ዙርያ ጠቃሚ የሆነ ግኝት ማግኘታቸው ይነገራል፡፡
ዶክተር ሞውራይስ ታይብ እ.ኤ.አ በ1996 የፈረንሳይ ብሄራዊ የሳይንስ ምርምር ማዕከል አካል በሆነው አይክስ ማርሴል ዩኒቨርሲቲ አባል በመሆን የስነ-ምድር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ቅድመ ታሪክ ጥናት እና የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያቶች በተመለከተ ጥልቅ ጥናቶች ያካሄዱ ተመራማሪ ናቸው።
ዶክተር ሞውራይስ ታይብ የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር ሆነው ማገልገል የቻሉም ናቸው።