
በሀገሪቱ ትዳሩ ያልተስማማቸው ሴቶች የሰርግ ወጪን ከፍለው የመፋታት መብት አላቸው
በፍቺ ለተጠናቀቁ ትዳሮች ሞቅ ያለ ድግስ የሚደገስባት ሞሪታንያ
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሪታንያ ከሌሎች ሀገራት ለየት ያለ ባህል ያላት ሀገር ነች፡፡ ከነዚህ መካከልም ትዳራቸውን በፍቺ ላጠናቀቁ ሴቶች ሞቅ ያለ ድግስ መደገስ አንዱ ነው፡፡
አምስት ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ያላት ሞሪታንያ ከፍተኛ ፍቺ ከሚፈጸምባቸው ሀገራት መካከልም አንዷ ናት፡፡
በዚች ሀገር ባህል መሰረት አግብተው የፈቱ ሴቶች ገና ካላገቡት ይልቅ በወንዶች ተፈላጊ ሲሆኑ ይህም ያገቡት የተረጋጋ ትዳር ለመምራት ይጠቅማሉ፣ ችግር የመፍታት ልምድ አላቸው እንዲሁም ቤትን በጥበብ የመምራት ልምድ እንዳላቸው ይታሰባል፡፡
ይህን ተከትሎም አግብታ የፈታች ሴትን በድግስ እና በደስታ የመቀበል ባህሉ እያደገ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
ያገቡ ሴቶች የበለጠ ተፈላጊ መሆናቸው ደግሞ ፍቺ እንዲበዛ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል፡፡
እንዲሁም አንዲት ሴት ትዳሯን በመፍታቷ እንዳይከፋት በሚል ሴቷን በድግስ መቀበል ተለምዷል፡፡
ትዳሯን ለፈታች ሴት በሚዘጋጀው ድግስ ላይ ከምግብ እና መጠጥ ባለፈ የሴቷን ውበት እና ስነ ልቦናዋን ከፍ የሚያደርጉ የስነ ጽሁፍ ዝግጅቶችም ይቀርቡበታል ሲል ቲአርቲ ዘግቧል፡፡
በተለይም የቀድሞ ባል እሷን በመፍታቱ እንዲጸጸት እና ዳግም ወደ እርቅ እንዲመጡ የሚያደርጉ ይዘቶችም ይቀርቡበታልም ተብሏል፡፡
እንዲሁም ይህ ሞቅ ያለ ድግስ ትዳሯን የፈታችው ሴት በቀጣይ ባል የሚሆናትን ወንድ ለመተዋወቅም እንደ ጥሩ እድል ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
በጓደኞቿ እና የቅርብ ቤተሰቦቿ የሚዘጋጀው ይህ ድግስ ህይወት እንደሚቀጥል፣ በቀጣይ የተሻለ እድል ሊገጥማት እንደሚችል ማሳያ ተደርጎም ይቆጠራል፡፡
ይሁንና ዝግጅቱ በትዳር መካከል የሚወለዱ ልጆችን ሊጎዳ ይችላል፣ የኢኮኖሚ ድቀት እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳቶችን ያደርሳል በሚል ከስነ ማህበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች ትችት ገጥሞታል፡፡
ሀገሪቱ ሴቶች በትዳር ውስጥ ምቾት ካልተሰማቸው በሰርግ ወቅት የወጣ ወጪን እና ለጥሎሽ የወጡ ወጪዎችን በመክፈል ወደ ቤተሰቦቿ ቤት እንድትመለስ የሚፈቅድ ህግንም ትከተላለች፡፡
የነዳጅ እና ብረት ማዕድን ሀብታም እንደሆነች የምትገለጸው ሞሪታንያ አብዛኛው ህዝቧ በግብርና ዘርፍ እና በድህነት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡