በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ማውርታኒያ የውድድሩን የ2019 አሸናፊ አልጀሪያን በማሸነፍ ታሪካዊ ድል ተቀዳጅታለች
ማውርታኒያ አልጀሪያን በማሸነፍ ታሪካዊ የተባለ ድል ተቀዳጀች።
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ማውርታኒያ የውድድሩን የ2019 አሸናፊ አልጀሪያን በማሸነፍ ታሪካዊ ድል ተቀዳጅታለች።
አልጀሪያን 1-0 ያሸነፈችው ማውርታኒያ ወደ መጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች ውስጥ በመካታት ታሪክ መስራት ችላለች።
ማውርታኒያ ያለፉትን ስምንት አህጉር አቀፍ የመጨረሻ ውድድሮችን አሸንፋ አታውቅም ነበር።
ነገርግን ያሉ ደላሂ በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠራት ግብ፣ አልጀሪያውያን ለሁለት ተከታታይ ጊዜ እንዲሸነፉ እና ከውድድሩ በጊዜ እንዲሰናበቱ አድርጓቸዋል። አልጀሪያ በ2ዐ21ም ተመሳሳይ ውድቀት አጋጥሟት ነበር።
ማውርታኒያ ባለችበት ምድብ 'ዲ' ውስጥ አንጎላ በሰባት ነጥብ እና ቡርኪናፋሶ በአራት ነጥብ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ወደ 16ቱ የመጨረሻ ቡድኖች ውስጥ ተካተዋል።
ማውርታኒያ ሳትጠበቅ አልጀሪያን በማሸነፍ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ይዛለች።
አልጀሪያ በሁለት ነጥብ አራተኛ ሆናለች።
አልጀሪያ ከማውርታኒያ ጋር በነበራት ጨዋታ አምበሉን ሪያድ ማህሬዝን ተቀያሪ ወንበር ላይ አድርጋው የነበረ ቢሆንም ውጤቱን ለመቀየር በሁለተኛው አጋማሽ ላይ አስልፋው ነበር። ነገርግን ይህ ጥረቷ ውጤት አልባ ሆኖባታል።
በሌሎች የትናንት ጨዋታዎች አንጎላ፣ካሜሩን እና ሴኔጋል ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
አንጎላ ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀችው ቡርኪናፋሶን 2-0 በማሸነፏ ነው።
ካሜሩን እና ጋምቢያ ያደረጉት ጨዋታ፣ በካሜሩን 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም ካሜሩን ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችላለች።
ሴኔጋል እና ጊኒን ያደረጉት ጨዋታ በሴኔጋል 2-ዐ አሸናፊነት ተጠናቋል፤ ሁለቱም ቡድኖች ወደ መጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች ውስጥ መካተት ችለዋል።
እስካሁን በተካሄዱ ጨዋታዎች 8 ቡድኖች ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችለዋል።
በስድስቱ ቡድኖች ከተደለደሉት ውስጥ ሁለት ምረጥ ቡድኖች እና አራት ምርጥ ሶስተኛ ሆነው የጨረሱ ቡድኖች የመጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች ይሆናሉ።
በርካታ ትላልቅ ስም ያላቸው ቡድኖች ወደዚህ ዙር የመካተት እድላቸውን እያጡ ናቸው።