በ6 ደቂቃ ብራዚላዊውን ሮናልዶ በልጦ ከፖርቹጋላዊው ሮናልዶ ክብረወሰን የተቃረበው ምባፔ
የ26 አመቱ ፈረንሳዊ በሪያል ማድሪድ የመጀመሪያ አመት ቆይታው በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረ አራተኛው ተጫዋች ሆኗል

ኪሊያን ምባፔ ለሎስ ብላንኮዎቹ በሁሉም ውድድሮች ያስቆጠራቸውን ጎሎች ቁጥር 31 አድርሷል
ፈረንሳዊው የሪያል ማድሪድ አጥቂ ኪሊያን ምባፔ በ28ኛው ሳምንት የስፔን ላሊጋ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ከክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ኮከቦች አንዱ ሆኗል።
በስፔኑ ክለብ አጀማመሩ ጥሩ ያልነበረው ምባፔ ትናንት ምሽት በስታዲዮ ደ ላ ሴራሚካ በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ ያስቆጠራቸው ጎሎች ሎስ ብላንኮዎቹን ለድል በማብቃት በሶስት ነጥብ ልዩነት ላሊጋውን እንዲመሩ አድርገዋል።
በ2024/25 የውድድር አመት ለሪያል ማድሪድ በሁሉም ውድድሮች 44 ጊዜ የተሰለፈው ምባፔ 31 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
ይህም በአውሮፓ አምስት ታላላቅ ክለቦች ውስጥ ለተከታታይ ስድስት አመታት ከ30 በላይ ጎሎችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ፈረንሳዊ ተጫዋች አድርጎታል።
የ26 አመቱ አጥቂ በሪያል ማድሪድ የመጀመሪያ አመት ቆይታ በርካታ ጎሎች ካስቆጠሩ አራት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል።
ምባፔ በስፔኑ ክለብ የመጀመሪያ አመት ቆይታው (2002/2003) 30 ጎሎች ያስቆጠረውን ብራዚላዊ አጥቂ ሮናልዶ ናዛሪዮ ደ ሊማ መብለጥ ችሏል።
ፖርቹጋላዊ ክርስቲያኖ ሮናልድ (በ2009/10)፤ ሆላንዳዊው ሩድ ቫኒስትሮይ (በ2006/07) ለማድሪድ እኩል 33 ጎሎችን አስቆጥረዋል። ምባፔ የሮናልዶ እና ቫኒስትሮይን ክብረወሰን ለመጋራት ሁለት፤ ለመስበር ደግሞ ሶስት ጎሎች ብቻ ይቀሩታል።
ቺሊያዊው ኢቫን ዛሞራኖ በመጀመሪያ አመት የሪያል ማድሪድ ቆይታው (1992/93) ያስቆጠረውን የ37 ጎል ክብረወሰን እንደሚሰብርም እያሳየው የሚገኘው ብቃት አመላካች ነው ይላል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ምባፔ በሰጠው አስተያየት "ከሮናልዶ (ብራዚላዊው) እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ የበለጠ ጎል ባስቆጥር እኔ የተሻልኩ ተጫዋች ነኝ ማለት አይደለም፤ የመጀመሪያ አመት ቆይታየ ጥሩ ነው ማለት ነው፤ ብዙ ጎል ማስቆጠር በላሊጋ፣ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮፓ ዴ ላሬ ዋንጫ ሲታጀብ ይበልጥ ዋጋ ይኖረዋል" ብሏል።
የቀድሞው የፒኤስጂ ኮከብ ትናንት ቪያሪያል ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የላሊጋ ጎሎቹን ቁጥር 20 አድርሰዋል። ይህም ከባርሴሎናው ሮበርት ለዋንዶውስኪ በአንድ ግብ ዝቅ ያለው ነው።