የዩኤኢው ኤ.አይ. ዩኒቨርስቲ እና የእስራኤል ዌይዝማን የሳይንስ ተቋም የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና እስራኤል የሰላም ስምምነት ከደረሱ በኋላ የተደረሰ በአይነቱ የመጀመሪያ ስምምነት ነው
የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዋናነት በሰው ሰራሽ የማሰብ ችሎታ (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ዘርፍ ይተባበራሉ
የዩኤኢው ኤ.አይ. ዩኒቨርስቲ እና የእስራኤል ዌይዝማን የሳይንስ ተቋም የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሞሐመድ ቢን ዛይድ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርስቲ እና የእስራኤል ዌይዝማን የሳይንስ ተቋም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት ዛሬ እሁድ መስከረም 03 ቀን 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና በእስራኤል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የእንደዚህ ዓይነት ስምምነት ሲፈረም ይህ የመጀመሪያው ሲሆን ስምምነቱ የተማሪ ልውውጥ መርሃ ግብሮችን ፣ ኮንፈረንሶችን እና የጥናትና ምርምር እቅዶች እንዲሁም በተመራማሪዎቻቸው መካከል የመረጃ ልውውጥን ያካትታል ፡፡ ስምምነቱ በተጨማሪም ለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የጋራ የኦንላይን ተቋም ማቋቋምን ያካትታል ሲል የኤሚሬትስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ስምምነቱ በርቀት የተካሄደ ሲሆን የ ዩኤኢው ዩኒቨርሲቲ ሊቀመንበር እና የሀገሪቱ የኢንዱስትሪና የላቀ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ / ር ሱልጣን አል ጃበር እና የዌይዝማን የሳይንስ ተቋም ፕሬዝዳንት እና ፕሮፌሰር የሆኑት አሎን ቼን ተፈራርመዋል ፡፡
ዶ / ር አል ጃበር “እንደ ዌይዝማን የሳይንስ ኢንስቲትዩት ካሉ ታዋቂ ተቋማት ጋር ለመተባበር እድል ማግኘት የሚደነቅ ነው” ብለዋል ፡፡
ትብብሩ “ከኮቪድ -19 እስከ የአየር ንብረት ለውጥ” ያሉ አንዳንድ የዓለምን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ለመጠቀም ያለመ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የዌይዝማን የሳይንስ ተቋም ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አሎን ቼን በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት “ከዚህ ልዩ ፣ ፈር ቀዳጅ ተቋም ጋር በመተባበር እና የሰው ሰራሽ የማሰብ ችሎታን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን) አንድ ላይ የማሳደግ እድል በማግኘታችን በጣም ተደስተናል ፡፡ እንደ ‘ኒውሮሳይንቲስት’ ባለሙያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በዲጂታል ግዛት ውስጥ የሚዘረጋ የሰው አንጎል ኃይል እና ውስብስብነት ቀጣይ አካል እንደሆነ አምናለሁ ፤ እንድምታዎቹም ሰፊ ሲሆኑ በሕይወታችን እና በጤንነታችን እንዲሁም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው” ብለዋል፡፡ “ሳይንስ ድንበር አያውቅም” ያሉት ፕሮፌሰሩ “ሙሉ ተስፋ አለኝ ፣ ይህ ትብብር በቀጣናው ውስጥ ባሉ ሳይንቲስቶች መካከል የዚህ አገላለጽ አንፀባራቂ ምሳሌ ይሆናል እንዲሁም የሰውን ዕውቀት ድንበር ያራዝማል” ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህ ስምምነት የተደረሰው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና እስራኤል አጠቃላይ ግንኙነቶቻቸውን ለማስተካከል ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ከፈጸሙ ከአንድ ወር በኋላ ነው፡፡
ሀገራቱ የደረሱት ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል በኢንቨስትመንት ፣ በቱሪዝም ፣ በቀጥታ በረራዎች ፣ በፀጥታ ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በኢነርጂ ፣ በጤና አጠባበቅ ፣ በባህል ፣ በአካባቢ ፣ አንዳቸው በሌላኛቸው ሀገር ኤምባሲዎችን በማቋቋም እና በሌሎች የጋራ ተጠቃሚነት ዘርፎችም ላይ ወደ ትብብር እያመራቸው ይገኛል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ በ 2019 የተቋቋመው ሞሃመድ ቢን ዛይድ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ በዓለም የመጀመሪያው በምርምርና ጥናት ላይ የተመሠረተ የምረቃ-ደረጃ ዩኒቨርሲቲ ነው ፡፡ በአቡ ዳቢ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው በኮምፒዩተር ራዕይ (computer vision) ፣ በማሽን መማር (machine learning) እና በተፈጥሮ የቋንቋ ቅንብር ዘርፎች የኤምኤስሲ እና የፒኤችዲ ፕሮግራሞችን ይሰጣል ፡፡
በእስራኤል ሬሆቮት የሚገኘው የዌይዝማን የሳይንስ ተቋም ደግሞ በዓለም ላይ ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው ሁለገብ የምርምር ተቋማት አንዱ ሲሆን በአምስት ፋኩልቲዎች የማስተርስ እና የዶክትሬት ደረጃ ድግሪዎችን ይሰጣል፡፡