የሳውዲው መካ መስጅድ በ10 ቀናት ውስጥ በ25 ሚሊዮን ሰዎች መጎብኘቱ ተገለጸ
የዘንድሮው ረመዳን ጾም ከገባ 13ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል

ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ብቻ ከ5 ሚሊዮን በላይ የኡምራ ተጓዦች መካ መስጅድ ደርሰዋል ተብሏል
የሳውዲው መካ መስጅድ በ10 ቀናት ውስጥ በ25 ሚሊዮን ሰዎች መጎብኘቱ ተገለጸ፡፡
በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የረመዳን ጾም ከተጀመረ 13ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡
ጤነኛ የሆኑ እና አቅም ያላቸው የእስልምና ዕምነት አማኞች በሙሉ ይጾሙታል የሚባለው ይህ የረመዳን ወር የእስልምና ዕምነት ካሉት አምስት ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡
የሳውዲው መካ በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ስፍራዎች መካከል ዋነኛው ሲሆን አማኞች በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ መጎብኘት የሚፈልጉት ስፍራ እንደሆነም ይገለጻል፡፡
ይህን ተከትሎም ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ብቻ 25 ሚሊዮን የእስልምና አማኞች መካ መስጅድ ገብተው ሶላት ሰግደዋል ሲል አል አረቢያ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ መካን ከጎበኙ ጠቅላላ አማኞች መካከል 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያህሉ ከመላው ዓለም የተጓዙ የኡምራ ተጓዦች ናቸው፡፡
ወደ መስጅዱ የሚገቡ አማኞችን ለማስተናገድ ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞች ተሰማርተዋል የተባለ ሲሆን ከአራት ሺህ በላይ ያሉ የጽዳት ሰራተኞች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
በቀጣዮቹ ቀናት የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ይመጣል በሚልም የዘምዘም ውሃ የሚያቀብሉ 20 ሺህ ሰራተኞች ተዘጋጅተዋልም ተብሏል፡፡
የመካ መስጅድም ለአማኞች ምቹ እንዲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል የተባለ ሲሆን 8 ሺህ የድምጽ ማጉያዎች፣ የሙቀት መቆጣጠሪያ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች እንደተዘጋጁም ተገልጿል፡፡