የዘንድሮው ረመዳን ጾም መቼ ይጠናቀቃል?
የረመዳን ጾም ቀናት ለ29 ወይስ 30 ቀናት ይቆያል?

ሀገራት የረመዳን ጾም ቀናትን ለመወሰን ሁለት አይነት አቆጣጠሮችን ይከተላሉ
የዘንድሮው ረመዳን ጾም መቼ ይጠናቀቃል?
በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የረመዳን ጾም ከተጀመረ 11ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡
ጤነኛ የሆኑ እና አቅም ያላቸው የእስልምና ዕምነት አማኞች በሙሉ ይጾሙታል የሚባለው ይህ የረመዳን ወር የእስልምና ዕምነት ካሉት አምስት ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡
የካቲት 22 ቀን የተጀመረው የዘንድሮው የረመዳን የጾም መቼ ላይ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ቢሆንም ትክክለኛውን ቀን ለማወቅ ግን ቀናትን መጠበቅን አስገድዷል።
አማኞችን ከፈጣያቸው ጋር የበለጠ በማቀራረብ የሚታወቀው ይህ ጾም ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን ብዙ ጊዜ ጾሙ በ29 አልያም በ30ኛው ቀን ያበቃል።
የዘንድሮው የረመዳን ጾም በየትኛው ቀን እንደሚያበቃ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን ሀገራት የበዓሉ መከበሪያ ቀንን ለማወቅ ሁለት አይነት አቆጣጠሮችን ይከተላሉ።
እንደ ሳውዲ አረቢያ ያሉ ሀገራት የመጨረሻው የረመዳን ጾም መጠናቀቂያ ወይም በዓልን ለማወቅ የሸሪአ ጨረቃ እይታን የሚጠቀሙ ሲሆን እንደ ቱርክ ያሉ ሀገራት ደግሞ የስስነ ፈለክ ወይም አስትሮኖሚካል አቆጣጠርን ይከተላሉ።
ከሳውዲ አረቢያ በተጨማሪ ግብጽ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ሞሮኮ እና ሌሎች የአረብ ሀገራት በጨረቃ እይታ ላይ የተመሰረተ አቆጣጠርን ይጠቀማሉ።
ቱርክን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ የረመዳን በዓል ቀንን ለመወሰን የስነ ፈለክ ወይም አስትሮኖሚካል አቆጣጠርን ይከተላሉ።
በዚህም መሰረት የዘንድሮው ረመዳን በዓል መጋቢት 20 አልያም መጋቢት 21 ቀን እንደሚከበር ይጠበቃል ተብሏል።