የቶክዮ ኦሎምፒክ የሜዳሊያ ሰንጠረዥን እየመሩ ያሉ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
በዘንድሮው የቶክዮ ኦሎምፒክ ላይ ለሚያሸንፉ ስፖርተኞች 5 ሺህ ሜዳሊያዎች ለሽልማት ተዘጋጅተዋል
እስካሁን 40 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት መቻላቸው ተነግሯል
በጃፓን አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 32ኛው የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ ከተጀመረ ዛሬ 3ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
የቶክዮ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መጀመሩን ተከትሎም በርካታ ውድድሮች ፍጻሜ አያገኙ ሲሆን፤ በርካታ ሀገራም የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ጀምረዋል።
በዚህም መሰረት ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ቻይና የሜዳሊያ ሰንጠረዡን በ6 የወርቅ፣ 1 የብር እና 4 የነሃስ በድምሩ በ11 ሜዳሊያዎች በመምራት ላይ ትገኛለች።
አስተናጋጇ ጃፓን ደግሞ በ5 የወርቅ እና በ1 የብር ሜዳሊያዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ አሜሪካ በ4 የወርቅ፣ 2 የብር እና 4 የነሃስ በድምሩ በ10 ሜዳሊያዎች 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ደቡብ ኮሪያ በ2 የብር እና በ2 የነሃስ ሜዳሊያዎች 4ኛ ደረጃ ላ ስትቀመጥ፤ ሩሲያ ደግሞ በ1 የወርቅ፣ 4 የብር እና 2 የነሃስ ምዳሊያዎች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ጣሊያን፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ ሀንጋሪ እና ቱኒዚያ ደግሞ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከ6ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ያለውን ይዘዋል።
ቱኒዚያ 1 የወርቅ እና 1 የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአፍሪካ አህጉር የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስት መግባት የቻለች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆን ችላለች።
እስካሁን ባለው መረጃም 40 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት መቻላቸውን ከስፍራው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በዘንድሮው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ከ205 ሀገራት የተውጣቱ ከ11 ሺህ በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ከስፍራው ተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ 33 አይነት ስፖርታው ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ በውድድሩ ለሚያሸንፉ አትሌቶችም 5 ሺህ ሜዳሊያዎች ለሽልማት ተዘጋጅተዋል።