“በሀሰተኛ ሚዲያዎች በኩል የሚተኮስብኝ ጥይት አያሳስበኝም” - ትራምፕ
ሁለት የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ዶናልድ ትራምፕ “ሊገድለኝ ያሰበ አካል የሚተኩሰው በሀሰተኛ ሚዲያዎች በኩል ነው” ሲሉ ተደምጠዋል
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው በርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃንን “ሀሰተኛና ሙሰኞች” እያሉ ወርፈዋል
ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫም መገናኛ ብዙሃን ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን ሰንዝረዋል።
በትናንትናው እለትም በፔንሲልቫኒያ ሊቲትዝ ባደረጉት ቅስቀሳ “ሀሰተኛ ሚዲያዎች”ን ወርፈዋል።
ትራምፕ በመስታውት በተከበበ መድረክ ላይ ለ90 ደቂቃዎች ባደረጉት ቅስቀሳ “ልገደል የምችለው በመገናኛ ብዙሃን በኩል ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሁለት የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ““እኔን ለማግኘት የሆነ ሰው በሀሰተኛ ሚዲያዎች በኩል ሊተኩስብኝ ይችላል፤ ይህ ብዙም የሚያሳስበኝ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።
የ78 አመቱ አዛውንት ከቴሌፕሮምፕተር (የንግግር ጽሁፍ የሚያነብቡበት) ውጭ ያደረጉት ንግግር በቅስቀሳው የተገኙትን ጋዜጠኞች “እነዚህ የምትመለከቷቸው ሁሉ ሀሰተኛ ናቸው፤ አይታመኑም” ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ሲኤንኤን፣ ኤንቢሲ፣ ሲቢኤስ፣ ኤምኤስኤንቢሲን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎችን በስም እያነሱም “ሀሰተኛ ዜና አቅራቢዎች እና ሙሰኞች” ሲሉ ወቅሰዋል።
ትራምፕ ንግግራቸው የመገናኛ ብዙሃንን ያለአግባብ የፈረጀ ነው በሚል ትችት ሲያስነሳባቸው የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው ቃል አቀባይ ስቴቨን ቹንግ መግለጫ አውጥተው ለመከላከል ሞክረዋል።
ቃል አቀባዩ ትራምፕ በትናንቱ ንግግራቸው የተቃቀሙት ጆሯቸው ላይ ጉዳት ያደረሰ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸው ሲያሾፉና ሲቀልዱ በነበሩ መገናኛ ብዙሃን ላይ ነው ብለዋል።
ከዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ጋር የተፋጠጡት ዶናልድ ትራምፕ ከ2016 ጀምሮ ከበርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ጋር አይንና ናጫ ሆነው ቆይተዋል።
በዘንድሮው ምርጫም ለዴሞክራቶች አድልተዋል፤ ከጋዜጠኝነት መርህ የወጣ ተግባር ፈጽመዋል ያሏቸውን መገናኛ ብዙሃን ከመውቀስ ባሻገር በቅርቡ በሲቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ የ10 ቢሊየን ዶላር ክስ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደምም በሲኤንኤን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒውዮርክ ታይምስ እና ኤቢሲ ኒውስ ላይ የስማ ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል የሚሉና ከኢፍትሃዊነት ጋር የተያያዙ ክሶችን ማቅረባቸው አይዘነጋም።
ትራምፕ በትናንቱ የፔንሲልቫኒያ ቅስቀሳቸው ተቀናቃኛቸውን ካማላ ሃሪስን “ሙሰኛ”፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን “የማይገባው ምስኪን”፣ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ደግሞ “ትልቅ ከፋፋይና ችግር ፈጣሪ” ሲሉ ወርፈዋል።