ዜለንስኪ ወደ ዋሽንግተን እንዳቀኑ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ቤጂንግ ገብተዋል
የሩስያው ቁልፍ የደህንነት ሰው የጉብኝታቸው አላማ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ለመምከር ነው ተብሏል
ቻይና 10 ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ከሞስኮ ጎን ተሰልፋለች በሚል በምዕራባውያኑ ትወቀሳለች
ዜለንስኪ ወደ ዋሽንግተን እንዳቀኑ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ቤጂንግ ገብተዋል
የሩስያው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በቤጂንግ ድንገተኛ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
የሀገሪቱ የደህንነት ምክርቤት ምክትል ሊቀመንበር የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ አሜሪካ መግባታቸው እንደተሰማ ነው ወደ ቤጂንግ የዘለቁት።
ሜድቬዴቭ ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በፈገግታ ታጅበው ሲነጋገሩ የሚያሳይ ምስልንም በቴሌግራም ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
የደህንነት ምክርቤት ምክትል ሊቀመንበሩ ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር “ድንበር አልባ” ስትራቴጂካዊ ትብብርን የሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ነው ያነሱት።
የቻይና እና ሩስያን የኢኮኖሚ ትብብር ከፍ የሚያደርጉና የሁለቱን ሀገራት ገዥ ፓርቲዎች ግንኙነት የሚያጎለብቱ ነጥቦችም የውይይታቸው አንኳር ነጥቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሜድቬዴቭ 10 ወራት የደፈነው የዩክሬኑ ጦርነት ላይ ምክክር መደረጉንም ያንሱ እንጂ ቀድሞ ያልተነገረለት ጉብኝታቸው ዋነኛ አላማ ምን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከሜድቬዴቭና ሌሎች የልኡኩ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት የዩክሬንን ቀውስ ለማብረድ ሁሉም የጦርነቱ ተዋናዮች ሰከን ብለው ፖለቲካዊ መፍትሄን እንዲፈልጉ ማሳሰባቸው ተገልጿል።
በዩክሬኑ ጦርነት ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ መገለል የደረሰባት ሩስያ ከቻይና ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና የደህንነት ግንኙነት መስርታለች።
በጸጥታው ምክር ቤትም በሞስኮ ላይ ሊጣሉ የነበሩ ማዕቀቦችን ውድቅ በማድረግ ቤጂንግ አጋርነቷን አሳይታለች።
ሀገራቱ ከምዕራባውያኑ የሚቃጡ ጥቃቶችን በጋራ ለመመከትም በ2022 ተደጋጋሚ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
የዛሬው የዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ጉብኝት ዋነኛ አላማም ይህንኑ ሁለንተናዊ ትብብር ማጠናከርን አላማ ያደረገ መሆኑ ታምኖበታል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በዛሬው እለት ዋሽንግተን መግባታቸውም ለድንገተኛው የሜድቬደቭ ጉብኝት መነሻ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።