በህዝብ ውሳኔ ወደ ሩሲያ የተጠቃለሉ ግዛቶች ካልተመለሱ ድርድር እንደማይኖር ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ተናግረዋል
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠች።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዘጠኝ ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀረው ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናግድ ላይ ይገኛል።
ከሰሞኑ ዋሸንግተን ፖስት በዘገባው አሜሪካ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እንድትደራደር በሯን ልትከፍት ይገባል ማለቷን ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ምላሽ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር ትክክለኛ ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ይሁንና ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለድርድር የምትቀመጠው የዩክሬን ድንበር ወደ ነበረበት ከተመለሰ፣ በሩሲያ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የጉዳት ካሳ ከተከፈላቸው እና ተጠያቂነት የሚሰፍን ከሆነ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን በኩል በተነሳው የድርድር ቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በኬቭ ተገኝተው ከዩክሬን ፕሬዝዳንት እና ሌሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር መክረዋል።
አምባሳደር ሊንዳ እንዳሉት ዋሸንግተን ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
አሜሪካ ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ ለዩክሬን ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ለግሳለች።
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ዩክሬን ከሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ትቃት ለመመከት በሚል ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን እንደምትለግስም አስታውቃለች።