የአለማችን አጭሩ ዶክተር - ጋኔሽ ባራያ - የጽናትና ይቻላል ተምሳሌት
91 ሴንቲሜትር የሚረዝመው ጋኔሽ የማህበረሰቡ ይደርስበት የነበረው ማሳቀቅ የልጅነት ምኞቱን ከማሳካት አላገገደውም
የህክምና ትምህርት እንዳይከታተል የተጣለበትን እገዳም ፍርድቤት ተመላልሶ በማሻር ያፌዙበትን ሁሉ ህይወት በሚታደግ ሙያ ተሰማርቷል
የ23 አመቱ ህንዳዊ ጋኔሽ ባራያ በምድር ላይ የማይቻል ነገር የለም የሚለውን አባባል ማረጋገጫ ተምሳሌት ሆኗል።
በጉጃራት ታላጃ ታሉካ በተባለ አካባቢ የተወለደው ጋኔሽ እስከ አራት አመቱ ድረስ እንደማንኛውም ህጻን ጤናማ አስተዳደግ ነበረው።
በጭንቅላቱ መጠን ከፍ ማለትና በቁመቱ እድገት መቆም ግራ የተጋቡት ቤተሰቦቹም ወደ ህክምና ተቋማት ደጋግመው ቢወስዱትም ለውጥ ማየት አልቻሉም።
የቁመቱ ማጠር እና የጭንቅላቱ መጠን ማነስ በትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጭምር ጣት የሚጠቋቆሙበትና የሚዘባበቱበት ልጅ መሆኑ ቢረብሸውም በትምህርቱ ላይ ማተኮርን መረጠ።
ለተማሪዎቹ ሽሙጥ ቦታ ከመስጠት ይልቅ ዶክተር የመሆን ህልሙን ለማሳካት በትምህርቱ ላይ በረታ ይላሉ ወላጆቹ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ውጤት ሲገባ ግን ከትምህርት ቤት እስከ መንደሩ ያሰለቸው አድልኦ ዳግም ፈተና ሆነበት።
በዩኒቨርሲቲ ህክምና ለማጥናት ያቀረበው ጥያቄ በውጤቱ ሳይሆን በቁመቱ ውድቅ ተደረገበት፤ የህንድ የህክምና ምክርቤት 91 ሴንቲሜትር ቁመት ያለው ጋኔሽ ድንገተኛ ታካሚዎችን እንደልብ ተሯሩጦ ማከም አይችልም አለ።
ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ጋኔሽ ተስፋ አልቆረጠም፤ ከጉጃራት የትምህርት ቢሮ እስከ ግዛቱ ፍርድ ቤት ድረስ በመዝለቅ አቤቱታውን አሰማ።
የጉጃራት ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ጥያቄውን ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ አሳለፈ።
የያኔው ታዳጊ ግን ይግባኝ ጠይቆ በ2018 በህንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምኞቱን የሚያሳካበት ውሳኔ እንዲተላለፍ ታግሏል።
በ2019ም የህክምና ትምህርቱን ጀምሮ በቅርቡ ተመርቋል፤ ባሃቭጋር በተባለ አካባቢም ስራ መጀመሩን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
“ከልጅነቴ ጀምሮ የጓጓሁለትን ዶክተር የመሆን ምኞት በብዙ ፈተና አልፌ አሳክቸዋለሁ፤ አዎ እኔ የተለየሁ ነኝ፤ ግን እንደማንኛውም ሰው ደስተኛ ህይወት መምራትና ቤተሰቦቼን ማኩራት እፈልጋለሁ” ብሏል ጋኔሽ።
በትምህርት ቤት በጓደኞቹ ይደርስበት የነበረው ተጽዕኖ በስራ ባልደረቦቹና በታካሚዎች ጭምር ባይጠፋም ያሳለፈው ፈተና ብርታት ሆኖት ለበርካቶች ምሳሌ የሚሆን ተግባሩን ገፍቶበታል።