የሰማዩ አሳ ነባሪ - ባለ ሶስት ፎቁ አውሮፕላን
ከአየር ንብረት የተዋደዱ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል የተባለው አውሮፕላን 755 ሰዎችን እንዲያሳፍር ዲዛይን ወጥቶለታል
በኩዌት በተካሄደ ኤግዚቢሽን ላይ ለእይታ የቀረበው የአውሮፕላን ዲዛይን ትኩረትን ስቧል
ኦስካር ቪናልስ የተሰኘ የአቪዬሽን ዲዛይነር "የሰማዩ አሳ ነባሪ" የሚል ቅፅል ስም የተሰጠውን ግዙፍ አውሮፕላን ዲዛይን አስተዋውቋል።
ቪናልስ በኩዌት በተካሄደ የመጪው ጊዜ ትራንስፖርት ገፅታን የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ላይ የአውሮፕላኑን ዲዛይን ካሳየ በኋላም መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።
ባለሶስት ፎቁ (የቱሪስት፣ ቢዝነስ እና ፈርስት ክላስ) አውሮፕላን ካሟላው ነገር በመነሳት "በራሪ ሆቴል" የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል።
ከጂም እስከ መዋኛ ገንዳ ያለው የሰማዩ አሳነባሪ ለታዳሽ ሃይል ልማት ትኩረት የሰጠ ነው መባሉንም ዘ ሰን ዘግቧል።
የሃይል ፍጆታውንም ከኤሌክትሪክ፣ ከፀሀይ ሀይል እና ከነዳጅ እንዲያገኝ ነው ዲዛይን የወጣለት።
76.8 ሜትር የሚረዝመው አውሮፕላን በስአት 997 ኪሎሜትር መጓዝ እንዲችልም ዘመናዊ ሞተሮች ይገጠምለታል ብሏል የዲዛይኑ ባለቤት ኦስካር ቪናልስ።
የዚህ አውሮፕላን ፍጥነት ከኤርባስ 380 ወይም ቦይንግ 747 ጋር ሲወዳደር ብዙም ፈጣን የሚባል አይደለም።
ይሁን እንጂ አውሮፕላኑ 755 ሰዎችን አሳፈሮ በሰማይ የሚቀዝፍ መሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው ተነግሯል።
የአቪየሽን ጉዳዬች ተንታኞች በርካታ ሰዎችን የሚጭኑ አውሮፕላኖች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ይገልፃሉ።
ሰፔናዊው ዲዛይነር ያስተዋወቀው የአውሮፕላን ዲዛይንም በቅርብ አመታት ውስጥ እውን እንደሚሆን ይጠበቃል።