በሰዓት ከ6 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚከንፈው አዲሱ ሱፐር ሶኒክ አውሮፕላን
አውሮፕላኑ ከዚህ ቀደም 8 ሰዓት ይፈጅ የነበረውን የኒውዮርክ ለንደን በረራ ወደ 1 ሰዓት ዝቅ ያደርጋል
በ2030 ሰማይ ላይ ይታያል የተባለው አውሮፕላኑ ከድምጽ በ5 እጥፍ ይፈጥናል
የእንግሊዝ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚሰራ አዲስ አውሮፕላን ንድፍ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
አዲሱ አውሮፕላን "በብርሃን ፍጥነት" መብረር ይችላል የተባለ ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 2030 ሰማይ ላይ ልናየው እንደምንችልም ተገልጿል።
የእንግሊዝ ስፔስ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገርሃም ተርኖክ እንዳስታወቁት ኩባንያቸው ከአውስትራሊያ ጋር ሰዎችን ከአህጉር ወደ አህጉር ከ4 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማጓጓዝ የሚችል አውሮፕላን እየሰራ ነው።
አውሮፕላኑ "ሳይነርጂክ ኤር በሪዚንግ ሮኬት" የተባለ አዲስ ሃይፐርሶኒክ ሞተር የሚገጠምለት ሲሆን፣ ሞተሩም በሃይድሮጂን እና ኦክሲጅን ውህድ የሚሞላ መሆኑም ታውቋል።
አዲሱ ሃይፐርሶኒክ ሞተር አውሮፕላኑ በሰዓት ከ6 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ እንዲከንፍ ጉልበት የሚሰጠው ነው ተብሏል።
ይህም አውሮፕላኑ ከድምጽ በ5 እጥፍ ፍጥነት እንዲጓዝ የሚያስችለው መሆኑንም የእንግሊዝ የጠፈር ምርምር ማእከል አስታውቋል።
አዲሱ ሃይፐርሶኒክ አውሮፕላን በመደበኛ በረራ 8 ሰዓት ይፈጅ የነበረውን የለንደን ኒውዮርክ በረራ ወደ 1 ሰዓት ዝቅ ያደርጋል ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2030 ወደ በረራ እንደሚገባ የተነገረለት አውሮፕላኑ አሁን ካለው የአየር ትራንስፖርት በዋጋ ርካሽ እንዲሁም ከባቢ አየርን የማይበክል እንደሆነም ተነግሮለታል።