የስትራቶላውንች ኩባንያ ንብረት የሆነው አውሮፕላን፥ በካሊፎርኒያ ማጆቭ በርሃ ለ6 ሰዓታት የሙከራ በረራ አድርጓል
የአለማችን ግዙፉ አውሮፕላን ክብረወሰን የሆነ ረጅም የሙከራ በረራ ማድረጉ ተገለፀ።
ከአሜሪካ የእግርኳስ ሜዳዎች ያህል ይገዘፋል የተባለው ግዙፉ አውሮፕላን 220 ቶን የሚመዝኑ እቃዎችን የመጫን አቅም አለው መባሉን ኢንዲፐንደንት ዘግቧል።
የክንፎቹ ርዝመት 117 ሜትር የሚደርስው ግዙፍ አውሮፕላን ስድስት ሞተሮች እንዳሉትም ነው የተነገረው።
አውሮፕላኑ በካሊፎርኒያ ለ6 ሰዓታት የሙከራ በረራ ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይም የሃይፐርሶኒክ ሚሴኤሎችን ጭኖ በመሞከር እንደሚቀጥል የስትራቶላውንች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዛካሪ ከሬቮር ተናግረዋል።
ኩባንያው ከድምፅ ፍጥነት በበለጠ በሚምዘገዘጉ ሃይፐርሶኒክ አውሮፕላኖች በተመጣጣኝ ዋጋ ሰዎችን ወደ ጠፈር ለመውሰድም አቅዷል።
በ2019 የመጀመሪያውን የጠፈር ጉዞ ያደረገው ስትራቶላውንች፥ በዘርፉ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል ሃይፐርሶኒክ አውሮፕላኖችን እንደሚጠቀም አስታውቋል።
ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን የሚተኩሱ አውሮፕላኖች እንዳሏቸው ይነገራል።
አሜሪካም ከ2020 ወዲህ እጅግ ፈጣኖቹን ሃይፐርሶኒክ አውሮፕላኖች በማምረት ተጠምዳለች ነው የተባለው።