የአሜሪካው ሁቨር ዳም በድርቅ ምክንያት ኃይል ማመንጨት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ
በግድቡ ምክንያት የተፈጠረው ባህር የውሃ ይዞታ በእጅጉ መቀነሱም ተነግሯል
በድርቁ ምክንያት በግድቡ የተጠራቀመው ውሃ መጠን በእጅጉ መቀነሱም ነው የተነገረው
በምዕራባዊ አሜሪካ ያጋጠመው የከፋ ድርቅ የሁቨር ግድብን (ሁቨር ዳም) ኃይል ማመንጨት ከማይችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል ተባለ፡፡
ድርቁ በኮሎራዶ ግዛት የሚገኘውን ግድብ የውሃ ይዞታ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲያጣ ስለማድረጉ ተነግሯል፡፡
በዚህም ከግድቡ መብራትን ጨምሮ የመጠጥ ውሃን ያገኙ የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ችግር ላይ መውደቃቸው ነው የተነገረው፡፡
ሁቨር ታይቶ የማይታወቅ እክል ገጥሞታል ያሉት የኃይል ማመንጫው ኃላፊዎች ግድቡን ተከትሎ ተፈጥሮ የነበረው ሰው ሰራሹ የሚዐድ ሐይቅ 28 በመቶ ያህል መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ ይህ ግድቡ ከተገነባበት ከ1930ዎቹ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ነው፡፡
ሸለቋማው የኮሎራዶ ወንዝ አካባቢ ባለፉት 28 ዓመታት ለተከታታይ ድርቅ ተዳርጎ መቆየቱንም ነው ኃላፊዎቹ የተናገሩት፡፡
ግድቡ የተገነባበት የኮሎራዶ ወንዝ ለአሪዞና፣ ኔቫዳ እና አንዳንድ የሜክሲኮ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ ምንጭ ሆኖ ያለግላል፡፡ ለአሪዞና፣ ካሊፎርኒያ እና ኔቫዳ ከተሞች ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ሁቨር የአሜሪካ የምህንድስና እና የግንባታ አቅም መታያ መስታወት ነው በሚል ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ አሜሪካ ያኔ በአስከፊነቱ በሚጠቀሰው የዓለም ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ጊዜ የገነባችው ሲሆን በግዝፈቱ ከዓለማችን ቀዳሚ ሆኖ ሲጠቀስም ቆይቷል፡፡
ልክ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉ 24 ሰዓታትን ተሰርቶም ነው የአሜሪካ ተስፋ ለመሆን የበቃው፡፡
ሁቨር እስከመጨረሻው በሚሞላበት ጊዜ ከባህር ጠለል በላይ እስከ 365 ሜትር (1,200 ጫማ) ድረስ ውሃ መያዝ የሚችል ሲሆን አሁን ግን ለሁለት አስርታት በዘለቀው ድርቅ ሳቢያ በየሳምንቱ አንድ ጫማ ዝቅ እያለ ከ1,050 ጫማ በታች መውረዱ ይነገራል፡፡ ይህ በዚሁ ቀጥሎ የግድቡ የውሃ ይዞታ ወደ 950 ጫማ የሚወርድ ከሆነ የግድቡ ተርባይኖቹ ይቆማሉ፤ ለማንቀሳቀስም አይችልም። በዚህም ኃይል ማመንጨት የሚያቆም ይሆናል፡፡
ሆኖም የግድቡ የአስተዳደር አካላት ይህ እንዳይሆን እየሠራን ነው ማለታቸውን ሲ.ኤን.ኤንን ጨምሮ ፈራንስ24ን መሰል የውጭ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡