የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከ5 ወራት በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎት አግኝቷል
የዩኒቨርሲቲው መምህረን ኢንተርኔት ባለመኖሩ “የድህረ-ምርቃ ትምህርት” ለመስጠት ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል
በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ኢንተርኔት ተቋርጦ ቆይቷል
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሁሉም ካምፓሶች ከትላንት ምሽት ጀምሮ ኢንትርኔት አገልግሎት መለቀቁን የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው ክልሉን በሚመራው ህወሓትና በፌደራል መንግስት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ውጊያ ማምራቱን ተከትሎ ነበር፡፡ የፌደራል መንግስት ህወሓት በክልሉ የሚገኘውን የሰሜን እዝ በማጥቃት ክህደት ፈጽሟል በማለት በክልሉ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ከጀመረ በኋላ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር፡፡
የኢንተርኔት መቋረጥ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን መምህራኑ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
የኢንትርኔት አገልግሎት አለመኖሩ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ማለትም በአሪድ፣ዓይደር፣መለስ እና ዓዲ ሓቂ ካምፓሶች የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ተፅእኖ ፈጥረዋልም ነው ያሉት መምህራኖቹ፡፡
መምህራኑ “ኢንተርኔት ባለመኖሩ ምክንያት በተለይም የድህረ-ምርቃ ትምህርት ለመስጠት ተቸግረናል” ብለዋል፡፡ በጊዜ አፕዴት መደረግ የነበራቸው ሶፍትዌሮች አውትዴትድ መሆናቸውንም ጭምር፡፡
አሁን በዩኒቨርሲቲው የብሮድባንድ ኢንትርኔት መለቀቁ፤ በመማር ማስተማሩ ሂደት የራሱ የሆነ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም መምህራኖቹ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል ግጭቱን ተከትሎ እስካሁን የኢንተርኔት አገልግሎት ቢቋረጥም፤ ከሰብአዊ እርዳታ ስራዎች ጋር በተያያዘ በተመረጡ ተቋማት የኢንተረኔት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ ጥቅምት 24፤2013 የፌደራል መንግስት፣ ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቀ በኋለ ሁለቱ አካላት ወደ ውጊያ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበት ዘመቻ” ማካሄድ መጀመሩን ተከትሎ በተፈጠረ ውጊያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አጋጥሟል፡፡