የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ቃል አቀባይ ከሃገሪቱ የደህንነት ሹም ጋር በመሆን ሳዑዲ ገቡ
የኤርትራ እና የሳዑዲ ጥምር የሚኒስትሮች ካውንስል ትናንት በሪያድ መምከሩ የሚታወስ ነው
ባለስልጣናቱ በሪያድ በሚኖራቸው የአንድ ቀን ቆይታ በድንበር ግጭቱ ጉዳይ ይመክራሉ ተብሏል
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ትንሹ አባል አል ፈቂ ሱሌይማን በድንበር ግጭቱ ጉዳይ ለመምከር ሳዑዲ አረቢያ ገቡ፡፡
በዕድሜ ትንሹ የምክር ቤቱ አባል አል ፈቂ የምክር ቤቱ ቃል አቀባይም ናቸው፡፡
የሃገሪቱን የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር እና የደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩን አስከትለውም ነው ወደ ሪያድ ያቀኑት፡፡
ዛሬን ብቻ በሚዘልቀው የሪያድ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስለገቡበት የድንበር ግጭት እና ስላላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ለሳዑዲ ባለስልጣናት ያስረዳሉ፡፡
ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግራ ሰፊ መሬትን የእርሻ ቦታዎችን ሳይቀር ይዛለች፤ ንብረት አውድማለች አቃጥላለችም፡፡
የራሱን ሉዓላዊ ግዛት መልሶ መቆጣጠሩን እንጂ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛቶች እንዳልነካ ያስታወቀው የሃገሪቱ ጦር ከግዛቶቹ ሊለቅ የሚችልበት ምንም አይነት አግባብ እንደሌለ በመግለጽ ወታደሮቹን በስፍራው አስፍሯል፡፡
ከአሁን ቀደም ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው አስተያየታቸው የሰጡት አል ፈቂ ውሳኔው ፖለቲካዊ እንጂ የጦሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግን ሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ በነበረችበት ወቅት ወረራ እንደተፈጸመባት በመግለጽ የሱዳን ጦር ከሉዓላዊ መሬቶቿ ለቆ እንዲወጣ ጠይቃለች፡፡
የድንበር ጉዳዮችን የሚፈታ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመስራት ላይ ሳለ ይህ መሆኑ አግባብ እንዳይደለ በመግለጽም ለችግሩ ሰላማዊ እልባት መስጠት እንደሚያስፈልግም ደጋግማ ገልጻለች፡፡
የኤርትራ እና የሳዑዲ አረቢያ ጥምር የሚኒስትሮች ካውንስል ትናንት በሪያድ የመጀመሪያ ምክክሩን ስለማድረጉ አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡