የትምህርት ፖሊሲው “ህጋዊነት” በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጥያቄ አስነሳ
የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አለመጽደቁ የህግ ጥሰት አለበት?
ፖሊሲዎች ሲቀረጹ ከህገ-መንግስቱ ጋር መጣጣማቸው ሊታይ እንደሚገባ የህግ ባለሞያዎች ተናገሩ
የትምህርት ፖሊሲው “ህጋዊነት” በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጥያቄ አስነስቷል።
ባለፈው ሳምንት የትምህርት ሚንስትሩ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሲያቀርቡ በም/ቤቱ አባላት የትምህርት ፖሊሲው አጸዳደቅ ጥያቄ ተነስቶበታል።
- 86 በመቶ የአንደኛና 71 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው- ትምህርት ሚኒስቴር
- የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች “የትምህርት ክፍያ” በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ጥያቄ ተነሳበት
የካቲት 20፤ 2015 ዓ.ም. በሚንስትሮች ም/ቤት የጸደቀው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ወደ ተግባር መግባቱን ትምህርት ሚንስቴር ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች በደብዳቤ አሳውቋል።
ሞላ ፈለቀ (ዶ/ር) የተባሉ የም/ቤቱ አባል በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በነበረው ሀገራዊ ውይይት እንደተሳተፉ ገልጸው፤ የፖሊሲውን ይዘት ብቻ ሳይሆን የህግ ጥያቄም አንስተውበታል።
የም/ቤቱ አባል በዋናነት ቋንቋ የተመለከተ ፖሊሲ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ስልጣንና ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።
ፖሊሲው ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀጥሎ የሁለተኛ ቋንቋ መረጣ ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥር አለመሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ባለመካተቱ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ያለውን ፈተና ገልጸዋል።
“ለምሳሌ በሲዳማ አፉን የፈታ ህጻን ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ከአምስቱ [ቋንቋዎች] አንዱን ቢመርጥ ወይም ኦሮምኛን ቢመርጥ፤ በወላይተኛ አፉን የፈታ ተማሪ አማርኛን ቢመርጥ፤ እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያዊያን በምን የጋራ ቋንቋ ነው ሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችን በጋራ ሊመክሩ፣ ሊዘክሩና ሊግባቡ የሚችለው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የም/ቤቱ አባል በዚህ ሳያበቁም ፖሊሲው በሚንስትሮች ም/ቤት ብቻ ጸድቆ ገቢራዊ መደረጉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን ስልጣንና ኃላፊነት የሚጥስ ነውም ብለዋል።
ለዚህም የሚንስትሮች ም/ቤትን ስልጣንና ተግባር የሚደነግገውን የህገ-መንግስቱን አንቀጽ 77 በመጥቀስ ም/ቤቱ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን “ይነድፋል፤ ያስፈጽማል” የሚለውን አንስተዋል።
“ራሱ [የሚንስትሮች ም/ቤት] ያመነጨውን ፖሊሲ ራሱ ህግ አድርጎ ራሱ እንዴት ፈጻሚ ይሆናል? እንደዚህ አይነት ሀገራዊ ፖሊሲዎች በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርበው አለመጽደቃቸው አሳሳቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ” ብለዋል።
የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፖሊሲውን ህጋዊነት በሚመለከት “የፖለቲካ ችግር” ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ በመጥቀስ ከእርሳቸው በተሻለ የም/ቤቱ አፈ-ጉባኤ ያብራሩታል በሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አል ዐይን አማርኛም የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ሲጸድቅ የእንደራሴዎች ም/ቤት ስልጣን ተገፍቷል ወይ? ፖሊሲን የማጽደቅ ስልጣንና ኃላፊነት ያለው የትኛው ም/ቤት ነው? ሲል የህግ ባለሞያዎችን አነጋግሯል።
የህግ ባለሞያዎች ፖሊሲ የፖለቲካ ሰነድ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህጎች ምንጭ የሆነ፣ አንድ ፓርቲ ሀሳቡን ለመሸጥ የሚያዘጋጀውና አመለካከቱና አስተሳሰቡ የሚገልጽበት እንዲሁም በፓርቲ ጽ/ቤት የሚወጣ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም ፖሊሲዎች ህገ-መንግስቱን ታሳቢ አድርገው ሊወጡ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የህግ ባለሞያ ሆኑት ሞላልኝ መለሰ የትምህርት ፖሊሲው በሚንስትሮች ም/ቤት መጽደቅ እንደሚችል ተናግረዋል። በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ደግሞ ከፖሊሰው የተቀዱ ህጎች ቀርበው እንደሚጸቁም ተናግረዋል። ፓርላማው ያጸደቃቸውን አዋጆች ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ደንብና መመሪያዎችን ደግሞ በሚንስትሮች ም/ቤት እንደሚጸድቅ ገልጸዋል።
“ፖሊሲዎች ፖለቲካዊ አንደምታ አላቸው። የህዝብ ጥቅም ታይቶ፣ ህዝብም ውይይት አድርጎበት ሊወጡ ይችላል። ይሄ የሪኦት ዓለም ጉዳይ ነው። ማህበራዊ ስሪትንም የሚያይ ነው” ሲሉ የህግ አማካሪና ጠበቃ ቢንያም ከበረ ተናግረዋል።
የፖሊሲ ማሻሻያ ከሆኑ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መጽደቅ አለበት የሚሉት የህግ ባለሞያው፤ ለውጦች የፓርላማን ብቻ ሳይሆን የህዝብን ይሁንታ ማግኘት አለባቸውም ይላሉ።
ፖሊሲዎች ሲወጡና ሲጸድቁ “ምንድ ነው መሰረታዊ ለውጡ? ወይስ ቀድሞ ነበረውን ማስፈጸም ነው? የሚሉ ጉዳዮች አሟጋች ናቸው። ለምሳሌ ከ10ኛ ክፍል የሆነውን [ብሄራዊ ፈተና] 12ተኛ ክፍል ካለ መሰረታዊ ለውጥ ነው። ይሄ በአስፈጻሚው አካል አይሆንም” በማለት አብራርተዋል።
የፌደራል የስራ ቋንቋ በህገ-መንግስቱ የተደነገገ ሲሆን፤ በትምህርት ፖሊሲው የፌደራሉን የስራ ቋንቋ ማስተማር ግዴታ መሆን አለበት ሲሉ ሞላልኝ መለሰ ገልጸዋል።
የፖሊሲው አስተሳሰቦች ህገ-መንግስቱን የሚቃረኑ አሊያም የሚጋጩ ከሆነ ተፈጻሚ እንደማይሆኑ ህገ-መንግስቱን በመጥቀስ ገልጸዋል።
“ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ ህጎች ተፈጻሚነት የላቸውም” የሚሉት የህግ ባለሞያው፤ ጉዳዩ ለህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ መቅረብ እንዳለበት አስምረዋል።
“ትምህርትን ስናነሳ የምንነጋገረው ስለ አምስት ዓመታት ስርዓት ብቻ አይደለም። አንድ ፓርቲ ስልጣን ላይ ሚቆየው ለአምስት ዓመት ነው። የትምህርት ፖሊሲ በየአምስት ዓመቱ የሚቀየር ከሆነ ሀገር እየተገነባ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ ሰነዶች ከመጽደቃቸውና ስራ ላይ ከመዋላቸው በፊት ምን ስርዓት ልንከተል ይገባል የሚለውን ነገር በደንብ መፈተሽና መነጋገር ይጠይቃል" በማለት ሀሳብ ሰንዝረዋል።