86 በመቶ የአንደኛና 71 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው- ትምህርት ሚኒስቴር
ትምህርት ሚንስቴር የትምህርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ የአንድ ትውልድ እድሜን እንደሚጠይቅ ተናግሯል
የትምህርት ቤቶች ግንባታና ግብዓት ላይ ጥያቄ የቀረበለት ትምህርት ሚንስቴር "መንግስትን በጀት ጠይቁ" ብሏል
የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረበው ትምህርት ሚንስቴር በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ከትምህርት ጥራት እስከ ትምህርት ቤቶች ግንባታና ፍትኃዊነት ከትምህርት ፈተናና ምዘና እስከ አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ድረስ ጥያቄ ቀርቦለታል።
ያለፈው ዓመት የ12ተኛ ክፍል ማጠናቃቂያ ፈተና ውጤት የትምህርት ጥራት "ሰፊ ክፍተት" ማሳያ ተደርጎ ቀርቧል።
በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከወሰዱ አንድ ሚሊዮን ገዳማ ተማሪዎች ውስጥ ሦስት በመቶዎቹ ብቻ የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸው አይዘነጋም።
በትምህርት ምዘናና ጥናት የ80 በመቶ ተማሪዎች ውጤት ከ50 በመቶ በታች መሆኑ ተነስቷል።
- ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ዩንቨርስቲ እንደማይገቡ ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ
- ከ12 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ፈተናን እንዳልወሰዱ ተገለጸ
የም/ቤት አባላት የትምህርት ጥራትን ያመጣሉ ባሏቸው ጉዳዮችና ከተመረጡባቸው የምርጫ ክልሎች የሰበሰቧቸውን የህዝብ ጥያቄዎች ጠይቀዋል።
በተለይም የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የግብዓት አቅርቦት ችግርና የበጀት ስርጭት በዋናነት ጥያቄ ተነስቶበታል።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የትምህርት ሚንስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተቋማቸው አቅሙን ኦሟጦ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ "መንግስትን በጀት ጠይቁ" ብለዋል።
"መንግስት ያልሰጠንን በጎን የምናገኝበት ምንም አይነት መንገድ የለም። እነዚህ ነገሮች መስራት አለባቸው ከተባለ ከፌደራል መንግስቱ በሚደረጉ የበጀት ውይይቶች ም/ቤቱ ሊይዘው የሚገባ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ለመቀለብ 22 ብር ተብሎ በጀት ለመፅደቅ ሲቀርብ በ 22 ብር ማንም መብላት እንደማይችል ከታወቀ፤ የለም እንኳን ሰው ዶሮ ለመቀለበም አይበቃም ማለት አለባችሁ" ሲሉ መልሰዋል።
የም/ቤቱ የሰው ኃብት ልማ፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለሚንስትሩ የበጀት እጥረት ምላሽ "በጀት በቂ ካልሆነ በጊዜ መጠየቅ አለበት" በማለት ተናግረዋል።
"የበጀት እጥረት ካለ ገንዘብ ሚንስቴርን በማሳመን ካልተቻለ ደግሞ ም/ቤቱን አቤት ለማለት በጊዜ ነው መሆን ያለበት። ለትምህርት ሚንስቴር ጥቅል የሆነ በጀት ነው ወደኛ የሚመጣው እንጂ የተማሪ ቀለብ 15 ብር ነው ተብሎ አይመጣም። ስለዚህ ይህን ችግር ወደ ራሳቸሁ መውሰድና በወቅቱ መከራከር፤ መጠየቅ ነው ያለበት እንጂ ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል ማለት አንችልም" ሲሉ ምላሹ እንደማይዋጥ ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ካሏት 47 ሽህ ገደማ ትምህርት ቤቶች 99 በመቶዎቹ አመቺ አለመሆናቸውን የጠቀሱት ሚንስትሩ፤ ተሰራ ባሉት ምዘና አራት ትምህርት ቤቶች ብቻ ከፍተኛውን ደረጃ አሟልተዋል ብለዋል።
86 በመቶ የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 71 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፍፁም ከደረጃ በተታች እንደሆኑ ተናግረዋል።
በትምህርት ምዘናና ጥናት ውጤት ከ4ተኛ ክፍል 20 በመቶዎቹ፤ ከ8ተኛ ክፍል ደግሞ 12 በመቶዎቹ ብቻ በትምህርት ፖሊሲው የተቀመጠውን 50 በመቶ ውጤት አስመዝግልዋል።
ሚንስቴሩ ችግሩን ለማስተካከል የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን በሪፖርታቸው ያቀረቡት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ የትምህርት ጥራትን ለማስተካከል ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
"የትምህርት ስርዓት ጊዜ ወስዶ ከተበላሻ በኋላ መልሶ ለመጠገንም ልክ የዛኑ ያህል ጊዜ ይወስዳል። የዚህን ሀገር የትምህርት ስርዓት በአንድና ሁለት ዓመት የምንጨርሰዉና የምናሻሽለው ቢሆን እኮ ደስ ይለናል። የጉዳቱ ስፋት እኮ አንድ ትውልድ ነው። ሌላ ትውልድ እንዳይበላሽ ነው እንቅስቃሴ እያደረግን ያለነው። ማሻሻያዎቹ በአንድ ጊዜ ለውጥ ይወጣሉ ተብሎ መጠበቅ የለበትም" ብለዋል።
የትምህርት ሚንስትሩ ችግሮችን ለመፍታት በመደበኛ አካሄድ መፍታት ባለመቻላችን "ለየት ያለ እንቅስቃሴ" ለማድረግ ተገደናል ብለዋል።
ዝርዝር እቅድ እያወጣን ነው ያሉት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ መንግስት ብቻውን ለመስራት አቅም ስሌለው ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሰፊ ዘመቻ በመጪዎቹ ወራት እንደሚጀመር ገልፀዋል።
ሚንስትሩ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን በጋራ መስራት አለብን ሲሉም አስስበዋል።
እያንዳንዱ ትምህርት ቤት ያለውና የጎደው በዝርዝር እየተለየ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም መሰረታዊ ማሻሻል ለማድረግ የም/ቤት አባላትን ድጋፍ ጠይቀዋል።