ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ለ41 ዓመታት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁም ነገር ያበቁ እናት ናቸው።
የክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ስርዓተ ቀበር በዛሬው እለት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
የክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና የቀብ ስነ ስርዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የመነግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ቤተሰቦቻው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ነው የተካሄደው።
ከቀብር ስነ ስርዓቱ ቀደም ብሎም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የሽኝት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ባሳለፍነው እሁድ በ85 ዓመታው ከዚህ ኣለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል።
በCOVID-19 ተይዘው በጳውሎስ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆየተው ባሳለፍነው እሁድ ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም በ85 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡
አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ በመባል የሚታወቁት ክብርትዶ/ር አበበች በ1972 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮ ድርቅ ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁለት ህፃናትን በመያዝ አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበርን መመስረታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።
ክብርትዶ/ር አበበች ባለፉት 41 በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁም ነገር ያበቁ ሲሆን፤ በተለይዩ ድህነት ቅነሳ ፐሮግራሞች ከ1 ነጥብ 5 ሚልየን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሰጥተዋል።
በመሆኑም በተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ታላላቅ ሽልማቶችና እውቅናዎችን እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ በሰብአዊነት አግኝተዋል።
ክብርትዶ/ር አበበች ጐበና በ1928 ዓ.ም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ በግራር ጃርሶ ወረዳ በቶርበን አሼ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ሸበል አቦ በተባለች የገጠር መንደር ነው የተወለዱት።
በወቅቱ በነበረው ባህልና ልማድ ገና የ11 ዓመት ልጅ እንዳሉ ትዳር ለመያዝ የተገደዱ ቢሆንም፤ ቀረበላቸውን የጋብቻ ጥያቄ በብቸኝነት በመቃወም ወደ አዲስ አበባ ገቡ።
በአዲስ አበባ ስራን ሳይንቁ ከግለሰቦች ቤት ከማገልገል እስከ ምርት ክፍል ኃላፊነት ማገልገላቸውን የአበበች ጎበና የህጻናት ክብካቤና ልማት ማህበር መረጃ ያመለክታል።