በውድድር ላይ ከአፍሪካ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ብቻ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ላይ የተካተቱ ሀገራት ሆነዋል
የዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በአሜሪካዋ ኦሪጎን በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው አርብ የተጀመረው ይህ ውድድር እስከ ፈረንጆቹ 24 ቀን 2022 ድረስ በአሜሪካ ኦሪጎን ከተማ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ኢትዮያዊያን በሚሳተፉበት በዚህ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ዛሬ ከሰዓት የወንዶች ማራቶን ውድድር ይካሄዳል፡፡
በውድድሩ ላይ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ዛሬም በተጠባቂ ውድድሮች ቀጥሎ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወርቅ እንደምታመጣ የምትጠበቅበት ውድድሮች ይካሄዳሉ ።
ለሊሳ ደሲሳ፣ታምራት ቶላ፣ ሞስነት ገረመው እና ሴፋ ቱራ በዚህ የወንዶች ማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ሲሆን ከኬንያ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡
ውድድሩ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 10 ሰዓት ከ15ኛው ደቂቃ ላይ እንደሚጀመር ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረገጽ ላይ ተመልክተናል፡፡
ትናንት ምሽት በተካሄደው የሴቶች የ10 ሺህ ሜትር ሩጫ ለተሰንበት ግደይ ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቅቅ የመጀመሪያውን ወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ ኢትዮጵያ ስታገስገኝ ኬንያውያን አትሌቶች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
እንዲሁም መሽት 5 ሰዓት ላይ ደግሞ የ10 ሺህ ወንዶች ሩጫ ንጋት 11 ሰዓት ላይ ደግሞ የወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉም ተብሏል፡፡
እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ላይ የገቡ ሲሆን አሜሪካ በሁለት ወርቅ እንዲሁም ቻይና፣ፖላንድ፣ጃፓን እና ፔሩ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ከአፍሪካ በብቸኝነት ኢትዮጰያ እና ኬንያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ የገቡ ሀገራት ናቸው፡፡