አትሌቶቹ ካለሰንደቅ ዓላማ እንዲወዳደሩ የተፈቀደ ቢሆንም እሱም ተከልክሏል
የሩሲያ አትሌቶች ከሰሞኑ በአሜሪካ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የአትሌቲክስ ውድድር ላይ እንዳይሳተፉ ታገዱ።
የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የሩሲያ አትሌቶች በአሜሪካው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እንደማይሳተፉ ውሳኔ አስተላልፏል።
ውድድሩ የፊታችን አርብ የሚጀመር ሲሆን ለዘጠኝ ቀናት ይካሄዳል። በዚህ የስፖርት ሁነት ላይ 18 የሩሲያ አትሌቶች ካለሰንደቅ ዓላማቸው እንዲወዳደሩ ተፈቅዶ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን እንደማይወዳደሩ ይፋ ተደርጓል።
የሩሲያ ተወዳዳሪዎች በሻምፒዮናው እንዳይሳተፉ የተደረገው ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት መሆኑም ነው በምክንያትነት የተጠቀሰው። ካለሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ይወዳደራሉ ተብለው የነበሩት 18 አትሌቶችም እንዳይወዳደሩ ተወስኗል።
ይህ ውሳኔ ከሩሲያ አትሌቶች ባለፈም የቤላሩስ አትሌቶችን እንደሚመለከት ነው የተገለጸው፡፡ ዩክሬን እና ሩሲያ እያደረጉት ባለው ጦርነት ቤላሩስ ከሩሲያ ጎን መቆሟን ተከትሎ ነው የቤላሩስ አትሌቶች የተከለከሉት።
የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች ከውድድር እንዲታገዱ ውሳኔ የተላለፈው መጋቢት አንድ ነበር። በወቅቱ በቤልግሬድ በተካሄደው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ላይ የሀገራቱ ሳይወዳደሩ ቀርተዋል።
ከዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ባለፈም በአበረታች ቅመሞች መጠቀም ምክንያት የሩሲያ ስፖርተኞች በተደጋጋሚ ከውድድር መገታገዳቸው ይታወሳል።
አበረታች ቅመሞች ተጠቅመዋል የተባሉት የሩሲያ ስፖርተኞች ከመታገዳቸውም በላይ ካለሰንደቅ ዓላማ እንዲወዳደሩ የተደረጉም ነበሩ። ይህ መጀመሪያ ተግባር ላይ የዋለው በአውሮፓውያኑ 2015 ነበር።
ቀደም ሲል 73 አትሌቶች ካለሀገራቸው ሰንደቅ ዓላማ እንዲወዳደሩ የተፈቀደላቸውና ወደ ውድድር የገቡ ነበሩ። በዚህ ሳምንት ብቻ ደግሞ 18 አትሌቶች ካለሀገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ለውድድር ቀርበው ነበር።