የወንድ የዘር ፍሬ ስለ ወንዶች ጤና ምን ይነግረናል?
ጥራት ያለው የዘር ፍሬ ያላቸው ወንዶች ብዙ ዓመት የመኖር እድላቸው የሰፋ ነው ተብሏል

አነስተኛ የዘር ፍሬ ያላቸው ወንዶች በህይወት እና በጤና ከመኖራቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ተገልጿል
የወንድ የዘር ፍሬ ስለ ወንዶች ጤና ምን ይነግረናል?
ከሰሞኑ መቀመጫውን ዴንማርክ የደረገ አንድ የጥናት ተቋም የወንዶች የዘር ፍሬ ጤና እና ከአጠቃላይ ጤና ጋር ባለው ዝምድና ዙሪያ ያተኮረ የጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል፡፡
በሰው ልጆች ስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ያተኮሩ የጥናት ውጤቶች በሚወጡበት በዚህ አምድ ላይ የወጣው ጥናት እንደሚለው ከሆነ የወንዴ የዘር ፍሬ ጥራት ከወንዶች ጤና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡
ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል በተባለው በዚህ ጥናት ላይ እንደተገለጸው የተሻለ ጥራት ያለው የዘር ፍሬ ያላቸው ወንዶች ጤነኛ እና ረጅም እድሜ የመኖር እድላቸው ሰፊ ነው ተብሏል፡፡
ጥናቱ ለ50 ዓመታት ሲደረግ ነበር የተባለ ሲሆን የወንዴ ዘር ፍሬ መጠን መብዛት፣ የዘር ፍሬ አቀማመጥ፣ የዘር ፍሬ የመንቀሳቀስ አቅም እና ቅርጽ ዋነኛ የጥራት መለኪያዎች ሆነዋል፡፡
በተለይም የዘር ፍሬ ፈሳሽ መጠኑ በአማካኝ 120 ሚሊዮን እና ከዛ በላይ ያላቸው ወንዶች ከዚህ መጠን በታች ካላቸው ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ በትንሹ ሶስት ዓመት እና ከዛ በላይ በህይወት እንደሚኖሩ በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በኮፐንሀገን ዩንቨርሲቲ ሆስፒታል በተደረገው በዚህ ጥናት ላይ የተሳተፉት እና የቡድኑ አስተባባሪ ዶክተር ላርክ ፕሪክሰን ለዩሮ ኒውስ እንዳሉት አነስተኛ የዘር ፍሬ ያላቸው ወንዶች በህይወት የሚኖሩበት እድሜም አነስተኛ እንደሚሆን ጥናቱ ጠቁሟል ብለዋል፡፡
ጥናቱ በተለይም የወንድ የዘር ፈሳሽ ጥራት ከወንዶች አጠቃላይ ጤና ጋር ግንኙነት እንዳለው ማመልከቱም ተገልጿል፡፡
አነስተኛ የወንድ የዘር ፈሳሽ ያላቸው ሰዎች ብዙ መጠን ካላቸው ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ በአማካኝ ሰባት ጊዜ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ገብተው ተገኝተዋል፡፡
በመሆኑም የዘር ፈሳሻቸው አነስተኛ የሆኑ ወንዶች ከነሱ በተቃራኒው ከሆኑ ወይም ብዙ የዘር ፍሬ ካላቸው ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ በህይወት የመኖር እድላቸው አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጊዜያቸውን በጤና የማሳለፍ እድላቸውም አነስተኛ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡