በኢትዮጵያ ያለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጠን አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል - ተመድ
ተመድ፤ በኦሮሚያ ባለው ግጭት ምክንያት ርዳታ ለማድረስ መቸገሩም ገልጿል
በትግራይ አሁንም ርዳታ ማድረስ ያልተቻለባቸው ቦታዎች እንዳሉ ተመድ በሪፖርቱ አመላክቷል
በኢትዮጵያ ያለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጠን አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል ሲል የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ዩኤን ኦቻ) ገለጸ፡፡
ተመድ በትናንትናው እለት ባወጣው ሪፖርት በመንግስትና በህወሓት መካከል በህዳር ወር የሰላም ስምምነት ቢፈረምም አሁንም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው ሁኔታ የሚያስደነግጥ ነው ብሏል፡፡
ኦቻ ችግሩን ለማቃለል ርዳታ በማቅረብ በኩል የተለያዩ ጥረቶች ማድረጉን ገልጾ፤ ይሁን እንጅ በትግራይ እና በአፋር ክልሎች ያለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከፍተኛና አሳሳቢ መሆኑ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በታህሳስ ወር ምርመራ ከተደረገባቸው ሰዎች አንድ ሶስተኛው የሚሆኑ ህጻናት ፣ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው ማረጋገጡም ነው ኦቻ የገለጸው፡፡
ከህዳር ወር የሰላም ስምምነት በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ የሚሰጠውን ርዳታ እየጨመረ ቢመጣም አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም መድረስ እንዳልተቻለ ገልጿል ተመድ በሪፖርቱ፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከህዳር አጋማሽ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ምግብ፣ የጤና እና የመጠለያ ርዳታ የጫኑ ከ3ሺህ በላይ የርዳታ ተሸከርካሪወች ወደ ትግራይ ክልል መላኩም አስታውቋል።
በታህሳስ ወር የመጨረሻ ሳምንት ብቻ 368ሺህ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆችን የምግብ ርዳታ አግኝተዋልም ነው ያለው ሪፖርቱ፡፡
ከተመድ ጋር የሚሰሩ ድርጅቶች ከጥቅምት ወር ጀምሮ በትግራይ ውስጥ ርዳታ ከሚስፈልጋቸው 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 60በመቶ ለሚሆኑ ድጋፍ ማድረጋቸውንም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ደበበ ዘውዲ በኤርትራ አቅራቢያ ያሉ የድንበር አካባቢዎችን ጨምሮ ሌሎች የርዳታ ቡድኖች የማይችሉባቸው ቦታዎች መድረሳቸውን ገልጸው ወደ 81ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ምግብ መሰጠቱ ተናግረዋል፡፡
በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል ትግራይ፣አማራና አፋርን ጨምሮ ከ8 ሚሊየን በላይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የምግብ እርዳታ መደረጉን አቶ ደበበ ገልጸዋል፡፡
በህዳር ወር በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ለሁለት አመታት የዘለቀውን ጦርነት በማቆም ትግራይ ላይ የነበሩ የእርዳታ እና የአገልግሎት እገዳዎችን ማንሳቱ ይታወቃል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት በታህሳስ ወር በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የውሃ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ስራዎችን እንዲሁም ወደ ዋና ከተማዋ መቀሌ የሚደረጉ የንግድ በረራዎችን መመለሱ አይዘነጋም፡፡
በትግራይ ውስጥ ውጊያው ጋብ እያለ ቢመጣም በኢትዮጵያ ደቡባዊ ኦሮሚያ ክልል ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው ያለው ተመድ፤ ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚደረገው ርዳታ አስቸጋሪ መሆኑንም ገልጿል፡፡
በቀጠለው ግጭት ብዙ ሰዎች መፈናቀላቸውንና በዚህም እስከ ታህሳስ 30 ድረስ ከኦሮሚያ ክልል ከ14ሺህ በላይ ሰዎች ወደ አማራ ክልል መሰደዳቸው የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ዩኤን ኦቻ) አስታውቋል፡፡