ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ከተቆጣጠረቻቸው ቦታዎች ውስጥ 40 በመቶውን በሩሲያ መነጠቋን አመነች
ሩሲያ 60 ሺህ ገደማ ወታደሮችን በኩርስክ ማሰማራቷ ተገልጿል
ዩክሬን በኩርስክ በኩል ጥቃት የጀመረችው በምስራቅ ዩክሬን እየገሰገሰ ያለው የሩሲያ ጦር ወደኋላ እንዲያፈገፍግ በሚል ስሌት ነበር
ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ከተቆጣጠረቻቸው ቦታዎች ውስጥ 40 በመቶውን በሩሲያ መነጠቋን አመነች፡፡
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መልኩን እየቀያየረ ሲሆን በምስራቅ ዩክሬን ባለው የውጊያ ግምባር የሩሲያ ጦር በየዕለቱ ወደ ፕሮቭስካ ከተማ እየተቃረበ ይገኛል፡፡
ዩክሬን ቁልፍ የሎጅስቲክስ ማዕከል የሆነችው ፐሮቭስካ ከተማን በሩሲያ እንዳትያዝ በሚል በድንገት ሳይታሰብ ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት ጥቃት ከፍታ ነበር፡፡
ባሳለፍነው ነሀሴ ላይ በተጀመረው የኩርስክ ግዛት ጦርነት ዩክሬን ከ 1 ሺህ 200 በላይ ስፋት ያለው አካባቢን ተቆጣጥራለች፡፡
የዩክሬን ያልታሰበ የኩርስክ ጥቃት በርካታ ሩሲያዊንን ያስደነገጠ እንደነበር በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡
ይሁንና ሩሲያ እንደታሰበው በምስራቅ ዩክሬን በኩል የሰማራችውን ጦር ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ከማድረግ ይልቅ ወደ ፊት እንዲገፋ አድርጋለች፡፡
ፑቲን “የዩክሬን ጦርነት ዓለም አቀፋዊ እየሆነ ነው” አሉ
ዩክሬንም የኩርስክ ግምባር ዓለማው መክሸፉን በወቅቱ ገልጻ የነበረ ሲሆን ቦታውን እስከቻለችው ድረስ ተቆጣጥራ የመቆየት እቅድ እንዳላት አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ የኩርስክ ግዛትን መልሳ ለመቆጣጠር አዲስ ዘመቻ ጀምራለች የተባለ ሲሆን እስካሁን በዩክሬን ጦር ተይዘው ከነበሩ ቦታዎች ውስጥ 40 በመቶውን መልሳ መቆጣጠሯን ዩክሬን ገልጻለች፡፡
ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የዩክሬን ጀነራል ለሮይተርስ እንዳሉት ሩሲያ ኩርስክን ለመቆጣጠር 11 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ጨምሮ 60 ሺህ ገደማ ወታደሮችን አሰማርታለች፡፡
ዩክሬን የኩርስክን ግምባር ለመበታተን የአየር ላይ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ እንደሆነች የተናገሩት አዛዡ በተለይም የሎጅስቲክስ ማዕከላትን እና የትራንስፖርት መስመሮችን ኢላማ አድርጋለችም ብለዋል፡፡