ሜሲ ለአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አባላት የወርቅ ስማርት ስልኮችን ሊሸልም ነው
የ35 አመቱ ኮከብ ለ35 የቡድን አጋሮቹ በ24 ካራት ወርቅ የተሰሩ አይፎን ስልኮችን ነው በስጦታ የሚያበረክተው
በእያንዳንዱ ስልኮች ላይም የተጫዋጮቹ ስምና በአለም ዋንጫው የለበሷቸው መለያዎች ቁጥር ተጽፎበታል ተብሏል
አርጀንቲናዊው የአለማችን የእግር ኳስ ፈርጥ ሊዮኔል ሜሲ በኳታር ትልቁን ደስታ ለሰጡት የቡድን አጋሮቹ ልዩ ስጦታ አዘጋጅቷል።
ሜሲ ለውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ የወርቅ ስማርት ስልኮችን በትዕዛዝ ማሰራቱ ነው የተሰማው።
ተጫዋቹ 175 ሺህ ፓውንድ ወጪ በማድረግ 35 የወርቅ አይፎን ስልኮችን አዟል።
ስማርት ስልኮቹ እያንዳንዳቸው ጥራቱ 24 ካራት በሆነ ወርቅ የተሰሩ እጅግ ቅንጡ ስልኮች መሆናቸውንም ዘ ሰን ዘግቧል።
የፒ ኤስ ጂው አጥቂ በኳታር የአለም ዋንጫውን እንዳነሳ አብዝቶ የጠበቀው ድል እውን እንዲሆን የተረባረቡ የቡድን አጋሮቹን ምን የተለየ ስጦታ በመስጠት ሊያስደምማቸው እንደሚችል ሲያስብ ቆይቷል።
ይህንኑ ጉዳይም የወርቅ ስማርት ስልኮችን ለሚሰራው” አይዲዛይን ጎልድ” ዋና ስራ አስፈጻሚ ቤን ሊዮንስ አማክሮታል።
ሊዮንስ “የአይዲዛን ስልኮች ቋሚ ደንበኛው ሜሲ ከወርቅ ስአቶች የተሻል ስጦታ ሊያበረክትላቸው እንደሚፈልግ ነገረኝ፤ እኔም የወርቅ ስአቶቹን ለምን አንሰራቸውም አልኩት፤ ወዲያው ተስማማን” ይላል።
በትዕዛዙ መሰረትም ለ35ቱም የቡድን አጋር ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ስማቸው የተጻፈባቸው ስማርት ስልኮችን ሰርተን አጠናቀን በዚህ ሳምንት አስረክበነውል ነው ያለው ሊዮንስ።
የወርቅ ስማርት ስልኮቹ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አባላቱ በኳታሩ የአለም ዋንጫ የለበሷቸው መለያዎች ቁጥር ከስማቸው ቀጥሎ መስፈሩም ተገልጿል።
የሰባት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ባለፈው ሰኞ የፊፋ የ2022 ምርጥ ተጫዋች ተብሎ መሸለሙ ይታወሳል።