አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ለሀገሩ አርጀንቲና አሁንም የመጫወት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል
በኳታር የዓለም ዋንጫ ትናንት ሲጠናቀቅ በሊዮኔል ሜሲ የሚመራው የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ፈረንሳይን በመርታት ዋንጫውን ማንሳት ችሏል።
አርጀንቲና ትናንት ማሸናፏን ተከትሎም የሊዮኔል ሜሲ ሀገር ለ3ኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ማንሳት ችላለች።
አርጀንቲና ሶስት ጊዜ መርታ አቻ በሆነችበት ምሽት ሌዮኔል ሜሲ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ሊዮኔል ሜሲ ከ36 አመት በፊት ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ያሳካውን ክብር በደገመበት ምሽት የብራዚላዊውን ፔሌ የጎል አስቆጣሪነት ክብር ማሻሻል ችሏል።
የኳታር የዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች እና የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አምበል ሊዮኔል ሜሲ ጨዋታውን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት፣ "ይህ ስኬት በህይወት ዘመኔ ስፈልገው የነበረው ነው" ብሏል።
የዓለም ዋንጫን ማንሳት ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረ ህልሜ ነው ያለው ሜሲ፣ ይህንን በማሳካቱም ሰድተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጨዋታው በዚህ መልኩ መጠናቀቁ በጣም አስደናቂ ነው፣ እግዚአብሄር ይህንን ስኬት እንደሚሰጠኝ አውቅ ነበር፣ ሲልም ተናግሯል።
ወደፊት ከአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ጋር ስለሚኖረው ቆይታ ስናገርም "ራሴን ከ ብሔራዊ ቡድን አላገልም ፣ ሻምፒዮን ሆኜ መጫወቴን መቀጠል እፈልጋለሁ"ብሏል።
አርጀንቲና ከዚህ ቀደም በ1978 እና 1986 እና የዓከም ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችላ የነበረ ሲሆን፣ ትናንት የተጠናቀቀውን የ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫን በማሸነፍ 3ኛው የዓለም ዋንጫዋን ወደ ቦነስአይረስ ይዛ ተመልሳለች።