
ሀላንድ በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ በ94 ጨዋታዎች 84 ግቦችን በማስቆጠር ስሙን ማጻፍ ችሏል
የማችስተር ሲቲው አጥቂ ኤርሊንግ ሀላንድ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በ100 ግቦች ላይ በመሳተፍ አዲስ ታሪክ አስመዘገበ፡፡
በኢትሀድ በርካታ የግብ ሪከርዶችን እየሰባበረ የሚገኝው የ24 አመቱ የፊት መስመር ተጫዋች ቅዳሜ ሲቲ ከብራይተን 2-2 በተለያየበት ጨዋታ ነው አዲስ ታሪክ በስሙ ያጻፈው፡፡
ወጣቱ አጥቂ በአጭር ጊዜ ውስጥ በ100 ግቦች ላይ በመሳተፍ በእንግሊዛዊው አለን ሽረር ተይዞ የነበረውን የረጅም ጊዜ ክብረወሰን በ6 ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ማሳካት ችሏል፡፡
ሀላንድ በ94 ጨዋታዎች ላይ 84 ግቦችን እና 16 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻትቶ በማቀበል ነው የሪከርዱ ባለቤት የሆነው፡፡
አራት ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ ከሆነው የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ሲቲ ጋር አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ሀላንድ እንደ ቀደሙት የውድድር ዘመኖች ጎል ማምረት ተስኖታል፡፡
በሊጉ ሰንጠረዥ ከተፎካካሪነት ወደ አምስተኛነት የተንሸራተተው ሲቲ ወደ ውጤታማነት ለመመለስ እየታገለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ኖርዌያዊው አጥቂ ክብረ ወሰኖችን ለመስበር የሚያስችሉ ግቦችን አልተቸገረም፡፡
በዘንድሮው የውድድር አመትም በ28 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች 21 ግቦችን እና 3 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
ከሲቲ ጋር ባሳለፈው የመጀመርያ የውድድር አመት በፕሪምየር ሊጉ 36 ጎሎችን በማስቆጠር አለን ሺረር እና አንዲ ኮል በአንድ የውድድር አመት 34 ግቦችን በማስቆጠር ይዘውት የነበረውን ሪከርድ አሻሽሏል፡፡
በሊጉ በ48 ጨዋታዎች 50 ግቦችን በፍጥነት በማስቆጠርም ወጣቱ ተጫዎች በሊጉ መዝገብ ስሙን አስፍሯል፡፡
ሲቲ በቅዳሜው ጨዋታ አቻ መውጣቱን ተከትሎ በሚቀጥለው አመት በሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ እድሉ በጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል፡፡
ሀላንድ በቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ቀደም ብሎ መሪነቱን ወስዶ የነበር ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ የብራይተኑ ፔርቪስ ኢስቱፒያን በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ ጨዋታውን ቀይራለች፡፡
ማንችስተር ሲቲ በቀጣይ በኤፍኤ ዋንጫ ከበርንማውዝ ጋር የሚገጥም ሲሆን ይህ ጨዋታ ቡድኑ በዚህ የወድድር አመት ዋንጫ ለማንሳት ያለውን ብቸኛ እድል የሚወሰንበት ነው፡፡