ሜሲ የብራዚል ፖሊስ የአርጀንቲና ደጋፊዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ተቃወመ
“ደጋፊዎችን ባናረጋጋ ኖሮ የከፋ ቀውስ ይፈጠር ነበር፤ ከጨዋታው ይልቅ ያሳስበን የነበረው ረብሻው ነበር” ብሏል
አርጀንቲና በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ብራዚልን አሸንፋ መሪነቷን አጠናክራለች
አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ የብራዚል ፖሊስ በደጋፊዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ተቃውሟል።
በ2026 የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የብራዚል ብሄራዊ ቡድንን ለመግጠም ወደ ሪዮ ዴጄኔሮ ያመራው የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ከባለሜዳዎቹ ደጋፊዎች ጋር ተጋጭተዋል።
ብሄራዊ መዝሙር ሲዘመር የተጀመረው ጸብ ጨዋታውን ለ30 ደቂቃዎች እንዲራዘም አድርጎታል።
የተወሰኑ የአርጀንቲና ደጋፊዎች መቀመጫዎችን በመስበር እና በመወርወር ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ የብራዚል ፖሊስ እርምጃ ሲወስድ ታይቷል።
የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አምበሉ ሊዮኔል ሜሲ እና የቡድን አጋሮቹ ጸብ ወደተፈጠረበት የስታዲየሙ ክፍል በማምራት ሁኔታውን ለማረጋጋት መሞከራቸውም ተገልጿል።
ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን የሰጠው ሜሲ “ሁኔታውን በፍጥነት ባናረጋጋው ኖሮ የከፋ ቀውስ ይፈጠር ነበር” ብሏል።
“ፖሊስ ደጋፊዎችን እንዴት ሲመታ እንደነበር አይተናል፤ ነገሩን ለማረጋጋት ሞክረን ወደ መልበሻ ክፍል ተመልሰናል” የሚለው ሜሲ የብራዚል ፖሊስ የወሰደውን እርምጃ ኮንኗል።
“ምን እንደሚፈጠር አናውቅም፤ ስለቤተሰቦቻችን እና ደጋፊዎቻችን ስናስብ ነበር፤ ከጨዋታው በላይ ያሳስበን የነበረው በስታዲየም ውስጥ የተፈጠረው ብጥብጥ ነበር” ሲልም መናገሩን ቢቢሲ ዘግቧል።
አንዳንድ ተጫዋቾች ቤተሰቦቻቸው ረብሻ በተፈጠረበት የስታዲየሙ ክፍሎች መኖራቸውም በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ጭንቀት ፈትሮ እንደነበር ገልጿል።
የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አምበሉ ማርኪንሆስ ከአርጀንቲና ተጫዋቾች ጋር ብጥብጡን ለማረጋጋት ሲሞክር የታየ ሲሆን ሁኔታው “በጣም አስፈሪ ነበር” ብሏል።
የአርጅንቲናው ክለብ ቦካ ጁኒየርስ እና የብራዚሉ ፍሉሚኔስ በያዝነው ወር በኮፓ ሊበርታዶሬስ የዋንጫ ጨዋታ ሲገናኙም በዚሁ የብራዚል ስታዲየም ከባድ ረብሻ መፈጠሩ የሚታወስ ነው።
የትናንቱ ምሽት ብጥብጥ አንድ አርጀንቲናዊ ደጋፊን ክፉኛ ማቁሰሉ ከመነገሩ ውጭ ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር አልተገለጸም።
ረብሻው ተጫዋቾቹን ቢረብሽም አርጀንቲና ኒኮላስ ኦታሜንዲ በ63ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል አሸንፋ ወጥታለች።
የአምስት ጊዜ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ ብራዚል በሶስት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በተከታታይ ሽንፈት አስተናግዳ ስድስተኛ ደረጃን ይዛለች።
የ2026ቱን የአለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ሜክሶኮ እና ካናዳ በጥምረት ያዘጋጁታል።