ሜሲና ሮናልዶን ያገናኘው የሳዑዲ ጨዋታ ዓላማ ምንድን ነው?
በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያለው ፉክክር ከነዳጅ እና ቱሪዝም በዘለለ በስፖርትም ጭምር እየሆነ መጥቷል
አንድ የስታዲየም መግቢያ ትኬት 2.6 ሚሊየን ዶላር የተሸጠበት ጨዋታን 69 ሺህ ሰዎች ስተዲየም ገብተው ተመልክተዋል
የፈረንሳዩ ፒ.ኤስ.ጂ የሪያድ ከዋክብቶችን 5 ለ 4 በሆነ ውጤት ያሸነፈበት የትናት ምሽቱ የሳዑዲ አረቢያ ጨዋታ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ እንደነበር አይዘነጋም።
የፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ፒ.ኤስ.ጂ በየዓመቱ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲሁም መካከለኛው ምስራቅ ተጉዞ ጨዋታ ማድረግ የተለመደ ቢሆንም በቅርቡ አል ናሰርን የተቀላለቀለው የፖርቹጋለዊው ኮከብ ሮናልዶና ሜሲን መገናኘት ለየት አድርጎታል።
በተለይም በጨዋታው የዓለማችንን 12 የባሎንዶር ሽልማቶችን ጠራርገው የወሰዱት ሁለቱም ኮከቦች ግብ ማስቆጠራቸው ደግሞ የፒ.ኤስ.ጂ እና የሪያድ ከዋክብቶች (የአል-ሂላል እና የአል-ናስር ተጫዋቾች ) ጨዋታ ይበልጥ ማራኪ አድርጎት አልፏል።
- ክርስቲያኖ ሮናልዶን ከሊዮኔል ሜሲ ያገናኘው የሳዑዲ ጨዋታ በፒ.ኤስ.ጂ አሸናፊነት ተጠናቋል
- ፖርቹጋላዊው ኮከብ ሮናልዶ “ለአል-ናስር መፈረሜ በህይወቴ የምኮራበት ውሳኔ ነው” አለ
ጨዋታው ሜሲና ሮናልዶ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙበት ሊሆን እንደሚችልም በርካቶች ግምታቸው እያስቀመጡ ነው።
የዘመኑ የዓለማችን የእግር ኳስ ጠበብት የሆኑት ሜሲና ሮናልዶ በእንደዚህ አይነት ጨዋታ ሲገናኙ ለ37ኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
ይህ ብእንዲህ እንዳለ ሜሲና ሮናልዶን ያገናኘው ጨዋታ ሌላ አላማ ያለው ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ከዋክብቶች የተገኙበት ጨዋታ በቱርክ የሳዑዲ ከጋዜጠኛ ጀማል ካሹጊ ግድያ ጋር በተያያዘ የጠለሸውን የመንግስት ገጽታውን በስፖርት ለማጠብ የሚያስችለው አጋጣሚ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም አሁን በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያለው ፉክክር ከነዳጅ እና ቱሪዝም በዘለለ በስፖርትም ጭምር በመሆኑ ሳዑዲ አረቢያ እንደ ኳታር ስሟን ከስፖርት ጋር በተያያዘ ገናና ለማደረግ የምታደረግውን ጥረት አካል መሆኑ እየተገለጸ ነው።
ሳዑዲ አረቢያ ፖርቹጋላዊውን የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶን በ200 ሚሊዮን ዩሮ ያስፈረመችበት ሚስጥርም ይህ ነው ይላሉ የስፖርት መገናኛ ብዙሃን።
የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሃፊ ኢብራሂም አልካሲም በቅርቡ “ሮናልዶ በየሳምንቱ ሲጫወት እዚህ ስቴድየም ውስጥ የሚመለከቱት ህጻናት በየጊዜው ተነሳሽነታቸውን ይጨምራል፤ ስለዚህ የሮናልዶ መምጣት የእግር ኳስ ጥራታችንን ይጨምርልናል፣ ትውልድ ነው የሚገነባበት” ማለታቸው አይዘነጋም።
የሮናልዶ መምጣት ሌሎች ከዋክብት ወደ ሊጉ እንዲመጡ መንገድ ጠራጊ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላልም ነበር ያሉት ዋና ጸሃፊው።
ሳኡዲ መሰል ጨዋታዎች ማዘጋጀቷ በዓለም 58ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የሳኡዲ አረቢያ ፕሮፌሽናል ሊግ ደረጃ ከፍ የሚያደረግ እንደሚሆንም ይታመናል።