ክርስቲያኖ ሮናልዶን ከሊዮኔል ሜሲ ያገናኘው የሳዑዲ ጨዋታ በፒ.ኤስ.ጂ አሸናፊነት ተጠናቋል
ሮናልዶ በሳዑዲ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገ ሲሆን 2 ግቦችን አስቆጥሯል
አንድ የስታዲየም መግቢያ ትኬት እስከ 2.6 ሚሊየን ደላር በተሸጠበት ጨዋታ ሜሲም ኳስና መረብን አገናኝቷል
ክርስቲያኖ ሮናልዶን እና ሊዮኔል ሜሲ ያገናኘው የሪያድ ኮከቦች እና የፈረንሳዩ ፒ.ኤስ.ጂ ጨዋታ ትናንት ምሽት በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ተደርጓል።
በጨዋታው ላይ በቅርቡ ለሳዑዲ አረቢያው አል ናስር የፈረመው ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲየኖ ሮናልዶ በሪያድ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶን ከሊዮኔል ሜሲ ያገናኘው የሳዑዲ ጨዋታ በፒ.ኤስ.ጂ 5ለ4 አሸናፊነት መጠናቀቁም ተነግሯል።
በጨዋታው ላይ ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲየኖ ሮናልዶ ሁለት ጎሎችን ለሪያድ ከዋክብት ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ እና በዓለም ዋንጫው የወርቅ ጫማ አሸናፊው ኪሊያን ምባፔ ለፒ.ኤስ.ጂ ጎሎችን ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ብራዚላዊው ኔይማር ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።
በኪንግ ፉአድ ስታዲየም የተካሄደውን የሪያድ ኮከቦች እና የፒ.ኤስ.ጂ ጨዋታን 69 ሺህ ሰዎች ስተዲየም ገብተው መልከታቸው ተነግሯል።
ሁለቱ የእግር ኳስ ኮከቦችን ያገናኘውን ጨዋታ ለመመልከት የሳዑዲ ሪል ስቴት ባለቤት በ2.6 ሚሊየን ዶላር የስታዲየምመግቢያ ትኬት በጨረታ መግዛታቸው ተሰምቷል።
ባለሀብቱ የገዙት የስታዲየም መግቢያ ትኬት የሪያድ ኮከቦች እና የፒ.ኤስ.ጂ ተጫዋቾችን በመልበሻ ክፍል ውስጥ የማግኘት እድልን ያካተተ እንደሆነም ተነግሯል።
የአምስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ከተለያየ በኋላ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት ከአል ናስር ጋር ለ2 ዓመት የሚቆይ ኮንትራት መፈረረሙ ይታወሳል።
ሮናዶ በአል ናስር ቆይታው በዓመት 170 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፈለዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በእግር ኳስ ታሪክ የዓለማችን ውዱ ተከፋይ እንዳደርገውም ተመላክቷል።
የ37 አመቱ ፖርቹጋላዊ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ማንችስተር ዩናይትድ በስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሮናልዶ በማንችስተር ዩናይትድ በቆየባቸው ጊዜያት በ346 ጨዋታዎች 145 ጎሎችን በማስቆጠር ከክለቡ ታላላቅ ተጫዋቾች በቀደሚነት የሚመደብ ነው።