አለም በርዕደ መሬት ለተመታችው ሶሪያ ፈጣን ምላሽ ያልሰጠው ለምንድን ነው?
በሶሪያ የደረሰው ርዕደ መሬት ከ3 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ህይወት ቢቀጥፍም ፈጣን የሰብአዊ ድጋፎች እየቀረቡ አለመሆኑ ይነሳል
የአውሮፓ ህብረት ግን የሚነሳውን ወቀሳ አስተባብሏል
ለ12 አመታት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ሶሪያ ባለፈው ሳምንት ከባድ ርዕደ መሬት ደርሶባታል።
እስካሁንም ከ3 ሺህ 500 በላይ ዜጎቿ ህይወታቸው ተቀጥፏል
በምዕራባውያኑ ማዕቀብ የተጣለበት የበሽር አል አሳድ መንግስትም አለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያቀርብ መጠየቃቸን የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አውስቷል።
ይሁን እንጂ ሀገራትም ሆኑ አለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ትኩረታቸውን ቱርክ ላይ አድርገው ሶሪያን ዘንግተዋታል የሚሉ ቅሬታዎች ይደመጣሉ።
የአውሮፓ ህብረት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛው ዳን ስቶኔስኩ ግን የሚቀርበውን ወቀሳ ውድቅ አድርገዋል።
የህብረቱ አባል ሀገራት 50 ሚሊየን ዩሮ በማሰባሰብ ለደማስቆ ለማድረስ እየሰሩ መሆኑንም ነው ስቶኔስኩ ለሬውተርስ የተናገሩት።
ድጋፉ በመንግስትም ይሁን በተፋላሚ ሃይሎች ስር በሚገኙ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲደርስም እንሰራለን ብለዋል።
የጣሊያን መንግስት የላከው ከ30 ቶን በላይ የሰብአዊ ድጋፍ ትናንት ቤሩት መድረሱንና ወደ ደማስቆ እንደሚጓጓዝም ነው ያብራሩት።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራቱ በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ሳይገድቧቸው አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፎችን እንዲያደርሱ እያበረታታ ይገኛልም ብለዋል።
“ለአመታት ስንሰራ የኖርነው ይህን ሆኖ ሳለ ሶሪያን ዘንግታችኋል በሚል የሚቀርብብን ወቀሳ ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ሲሉም አክለዋል ልዩ መልዕክተኛው።
የበሽር አል አሳድ መንግስት አስቸኳይ ድጋፎቹ በቱርክ ድንበር በኩል የሚቀርቡ ከሆነ በተቃዋሚ ሃይሎች እጅ ይገባል በሚል በቀጥታ በደማስቆ በኩል እንዲቀርብ መጠየቁ ይታወሳል።
አንዳንድ ታዛቢዎችም “አል አሳድ ርዕደ መሬቱንም ፖለቲካዊ መልክ አስይዘውታል፤ የሰብአዊ ድጋፎች እየቀረቡ የሚገኙትም ታማኝ ሃይሎቻቸው በሚገኙባቸው አካባቢ ብቻ ነው” የሚል ወቀሳን እንደሚያነሱ ሬውተርስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ የአሳድ መንግስት ለዚህ ወቀሳ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
የአውሮፓ ህብረት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛው ዳን ስቶኔስኩ ግን “የሶሪያ መንግስት ሰብአዊ ድጋፎችን የማታለል” ልማድ ስላለው በቀጥታ ለተጎጂዎቹ እንደሚያደርስ ማረጋገጫ ሊሰጠን ይገባል ነው ያሉት።
የአረብ ሃገራት ድጋፍ
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሶሪያ እና በቱርክ በደረሰው ርዕደ መሬት ፈጣን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ምግብ ልካለች።
የዱባይ ገዢው ሞሃመድ ቢን ረሺድ አል ማክቱምም ለሶሪያ የ13 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ማዘዛቸው ተነግሯል።
የኦማን፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ እና አልጀሪያ መሪዎችም ለአል አሳድ ደውለው አጋርነታቸውን መግለጻቸውና የነፍስ አድን ባለሙያዎችን መላካቸውንም ሚድልኢስት አይ አስነብቧል።
የእርዳታ መስመር ክፍት ለማድረግም ምዕራባውያን እና የአሳድ መንግስትን የሚያቀራርብ ድርድር እየተካሄደ ነው ተብሏል።
ሶሪያ በአሌፖ፣ ሃማ እና ላታኪያ ያስተናገደችው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለ12 አመታት ሰላም የናፈቃቸውን ሶሪያውያን ሰቆቃ ይበልጥ አክፍቶታል።