ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬን ወታደር ጋር በተደረገ ትንቅንቅ በሰንጢ ለተዋጋው ወታደሯ "የሩሲያ ጀግና ሽልማት" ሰጡ
ሩሲያ ጦሯን ዘመናዊ መሳርያዎችን እንደምታስታጥቅ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ

ፕሬዝዳንቱ በዩክሬን እየተዋጉ ያሉ ወታደሮቻቸውን አሞካሽተዋል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬን ወታደር ጋር በተደረገ ትንቅንቅ በሰንጢ ለተዋጋው ወታደሯ "የሩሲያ ጀግና ሽልማት" ሰጡ።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን እየተዋጉ ላሉ የሩሲያ ወታደሮችን ያሞካሹ ሲሆን ሽልማትም አበርክተዋል።
አንድሬይ ግሪጎሪቭ የተሰኘው የሩሲያ ወታደር በዩክሬን ውጊያ ግምባር ልዩ ድል ተቀዳጅቷል በሚል "የሩሲያ ጀግና" የሚል ሽልማት ከፕሬዝዳንቱ እጅ ተረክቧል።
ወታደሩ ለሽልማት የበቃው በውጊያ ግምባር ከአንድ የዩክሬን ወታደር ጋር ያደረገው ትንቅንቅ እና ወታደሩን በሰንጢ ወግቶ የገደለበት ክስተት ነበር።
እነዚህ የሁለቱ ሀገራት ሁለት ወታደሮች ለረጅም ጊዜ ያደረጉት ፍልሚያ ፊልም የሚመስል ሲሆን በመጨረሻም የሩሲያው ወታደር የዩክሬን አቻውን አንገቱ ላይ በሰንጢ ወግቶ ገድሎታል ተብሏል።
ይህ ወታደር ላደረገው ተጋድሎ በፕሬዝዳንት ፑቲን ልዩ የጀግና ሜዳሊያ እንደተበረከተለት አርቲ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በዚህ የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በዩክሬን እየተዋጉ ያሉ የሩሲያ ወታደሮችን "ጀግኖች ናችሁ" ሲሉ አሞካሽተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ የሩሲያ ጦር ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እንደሚታጠቅም ተናግረዋል።
ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ወደ መቋጫው ላይ መድረሱን የሚያመለክቱ እየታዩበት ይገኛል።
በተለይም የዩክሬን ዋነኛ የገንዘብ፣ ጦር መሳሪያ፣ የዲፕሎማሲ እና ሌሎች ድጋፍ አድራጊ የነበረችው አሜሪካ ጦርነቱ እንዲቆም እያደረገች ትገኛለች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ የጦርነቱ ዋነኛ ተቃዋሚ እንደሆኑ እና መቆም እንዳለበት ሲናገሩ ነበር።
ይህን ተከትሎ የአሜሪካ እና ሩሲያ ተወካዮች የመጀመሪያቸውን ውይይት በሳውዲ አረቢያ ሪያድ አድርገዋል።
ጦርነቱን ለማስቆም ሁለተኛ ዙር ውይይት በቀናት ውስጥ ይካሄዳል የተባለ ሲሆን አውሮፓዊያን እና ኔቶ ግን ዩክሬን ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋታል እያሉ ናቸው።