ሜታ "ሞት ለካሚኒ" የሚሉ መልዕክቶችን ማጋራት ፈቀደ
የኩባንያው ቦርድ በዛሬው እለት ባሳለፈው ውሳኔ፥ ከዚህ ቀደም ከፌስቡክ ገፆች ይነሱ የነበሩት መፈክሮች ምንም አይነት ስጋትን አያመጡም ብሏል
ሩስያ በዩክሬን ጦርነት በጀመረች ማግስት "ሞት ለፑቲን" የሚሉ መልዕክቶችን ማጋራት መፈቀዱ ይታወሳል
የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ ፌስቡክ ለኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ሞትን የሚመኙ መፈክሮችን እንዳያነሳ ወስኗል።
የኩባንያው ቦርድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ክልከላ በዛሬው እለት ያነሳ ሲሆን፥ "ሞት ለካሚኒ" የሚሉ መፈክሮችን መለጠፍ ይቻላል ብሏል።
በሜታ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግለት ነገር ግን ገለልተኛ ነው የተባለው ቦርድ፥ መፈክሩ ግጭት የመቀስቀስ ሃይል የለውም ማለቱንም ሬውተርስ አስነብቧል።
"ሞት ለካሚኒ" የሚለው ሀረግ ባለፉት ወራት በኢራን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በማፈን ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት አያቶላህ አሊ ሃሚኒን መጥፎ ተግባርን የሚያመላክት እንጂ ግጭትን የሚቀሰቅስ አይደለም ብሏል ቦርዱ።
ኢራናውያን አገላለፁን የሚጠቀሙት ውድቀትን ለመመኘት ነው፤ የፓለቲካ መፈክር እንጂ የግድያ ዛቻ አይደለም የሚለውንም በምክንያትነት አስቀምጧል።
ኩባንያው በቀጣይ ከሀገራት መሪዎች ጋር የተያያዙ ይዘቶች የሚስተናገዱበት ስርአት እንዲያዘጋጅም ነው ያሳሰበው።
ኢራን ከመስከረም ወር ወዲህ የገባችበት አመፅ የግዙፉን ማህበራዊ ትስስር ገፅ ስራ ማብዛቱ ተነግሯል።
ኩባንያው አመፁን የሚያባብሱና ለንፁሃን ደህንነት አደጋ ይሆናሉ ያላቸውን ይዘቶች የማጥፋትና ተደራሽነቱን የመቀነስ ስራ ላይ መጠመዱንም ነው የገለፀው።
ሩስያ በየካቲት ወር በዩክሬን ከጀመረች በኋላ ሜታ ለፕሬዚዳንት ፑቲን ሞትን የሚመኙ ይዘቶች እንዲለጠፉ ፈቃድ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል።
ኩባንንያው ያስቀመጠውን ክልከላ በልዩ ሁኔታ ያነሳው "በፑቲን የወረራ ውሳኔ" የተበሳጩ ወገኖች ቁጣቸውን እንዲገልፁ እድል ለመስጠት መሆኑንም ማሳወቁ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ከቀናት በኋላ ይህን ፈቃዱን ለመሰረዝ ተገዷል።
ፌስቡክ በአሜሪካ ካፒቶል ሂል የትራምፕ ደጋፊዎች ካስነሱት አመፅ ጋር በተያያዘም የቁጥጥር ስርአቱ ጥያቄ ውስጥ መውደቁ ይነገራል።