ሜታ በትራምፕ ወደ ፌስቡክ መመለስ ላይ ውሳኔ ሊሰጥ ነው
ሜታ፤ ትራምፕ ወደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም እንዲመለሱ ለመፍቀድ እስከ ጥር 7 ድረስ ይወስናል ተብሏል
ትራምፕ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ መመለስ እንደማይፈልጉ በቅርቡ መግለጻቸው አይዘነጋም
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ ኩባኒያ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም እንዲመለሱ ይፈቀድላቸው እንደሆነ ለማሳወቅ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በማህበራዊ ሚዲያው በርካታ ተከታይ የላቸው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ወደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም እንዲመለሱ ለመፍቀድ እስከ ጥር 7 ድረስ እንደሚወስን ቀደም ሲል መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ይህ ውሳኔ አሁን ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ፋይናንሺያል ታይምስ ጉዳዩን የሚያውቅ ሰው ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ሜታ በጉዳዩ ላይ የሚያተኩር የስራ ቡድን አቋቁሟል ያለው ዘገባው፤ ቡድኑ ከፐብሊክ ፖሊሲ እና ኮሙዩኒኬሽን ቡድኖች እንዲሁም ከይዘት ፖሊሲ ቡድን የተውጣጡ ሰራተኞችን ያካተተ መሆኑን ገልጿል።
የሮይተርስ ዘግባ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሜታ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
የትራምፕ ጉዳይ እንደገና ተመርምሮ ውሳኔ እንዲተላለፍበት የተፈለገው የትዊተር አዲሱ ባለቤት ኢሎን መስክ ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይ በትራምፕ ላይ የጣሉት ቋሚ እገዳ፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እርምጃውን በመቃወም የድጋፍ ድምጽ ከሰጡበት በኋላ መሰረዙን ተከትሎ ነው፡፡
በተሰበሰበው የህዝብ አስተያየት መሰረት ከ15 ሚሊዮን (51.8 በመቶብ) በላይ የሚሆኑ የትዊተር ተጠቃሚዎች ትራምፕ ወደነበሩበት እንዲመለሱ የድጋፍ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
ትዊተርን ጨምሮ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የትራምፕ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ መመለስ ቢሹም ግን ትራምፕ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
በቅርቡ በነበረው በሪፐብሊካኑ የአይሁድ ጥምረት አመታዊ የአመራር ስብሰባ ላይ ወደ ትዊተር ለመመለስ ማቀዳቸውን የተጠየቁት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በቪዲዮ ሲናገሩ "ለዚህ ምንም ምክንያት አይታየኝም" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ከትዊተር፣ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ይልቅ የተሻለ ተሳትፎ በሚያደርጉበት በትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ በተዘጋጀው አዲሱ ፕላትፎርም “ትሩዝ ሶሻል አፕ” ላይ እንደሚቆዩም ተናግረዋል።
እንደፈረንጆቹ በ2024 ወደ ነጩ ቤተመንግስት ዋይት ሀውስን በድጋሚ ለመመለስ ጉዞ ላይ የሚገኙት ትራምፕ ኢሎን መስክንና ኩባኒያው ወሳኔ ቢያሞካሹም በትዊተር ከበቂ በላይ መሰቃየታቸው ገልጸዋል፡፡