“ትሪድስ” ትዊተርን የሚገዳደር አዲሱ የሜታ ኩባንያ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ይፋ ተደረገ
“ትሪድስ” እድሜው ከ12 ዓመት በላይ የሆነ ሰው በኢንስታግራም አካውንቱ በመግባት መጠቀም ይችላል
አዲሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ “ትሪድስ” ለጊዜው በአፕ ስቶር የተለቀቀ ሲሆን፤ በ100 ሀገራት ውስጥ ይሰራል ተብሏል
የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ ትዊተር የሚፎካከር አዲስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያውን ሌሊቱን ይፋ አድርጓል።
“ትሪድስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያ በጽሁፍ ሃሳብ መለዋወጫ መድረክ መሆኑንና ከኢንስታግራም ጋር እንደሚቆራኝ ሜታ ገልጿል።
የፌስቡክ መስራችና የሜታ ኩባንያ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ “ትሪድስ አሁን እዚህ ነው፤ እንጠቀምበት” የሚል መልእክት አስተላልፏል።
ማርክ ዙከርበርግ “ትሪድስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ሰዎች አንድ ላይ በመምጣት ስለ ዛሬ እንዲሁም ስለ ነገ ጉዳዮቻቸው የሚወያዩበት መድረክ ነው” ብሏል።
የትሪድስ የማህበረዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ልክ እንደ ማንኛውም ገጽ ክርኤተሮችን መከተል እና በቀጥታ መገናኘት ያስችላል የተባለ ሲሆን፤ የራሳቸው ተከታዮችንም ማፍራት ይችላል ተብሏል።
የትሪስድ መተግበሪያ አሁን ላይ በአፕ ስቶር ላይ ተለቋል የተባለ ሲሆን፤ እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ የኢንስታራም ተጠቃሚዎች በኢንስታራም አካውንታቸውን ተጠቅመው ወደ ትሪድስ መግባት ይችላሉ።
አዲሱ ትሪድስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ለጊዜው በ100 ሀገራት ጥቅም ለይ ውሏል ያለው ሜታ ኩባንያ፤ ከቁጥጥር ስጋት ጋር በተያያዘ በተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት ላይ እንደማይሰራም አስታውቋል።
ሜታ ኩባንያ በይፋ ወደ ስራ ያስገባው አዲሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያ (ትሪድስ) ምንም አይነት ገደብ የሌለበትና በነጻ የሚቀርብ ነው ተብሏል።
ይህም አገልግሎቶቹን እየገደበ እና በክፍያ እያደረገ ያለውን ትዊተር ደንበኞች ለማስኮብለል ሊረዳው እንደሚችል ተገምቷል።