ሜታ ትዊተርን የሚገዳደር አዲስ መተግበሪያውን ከነገ በስቲያ ስራ ያስጀምራል
“ትሪድስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው መተግበሪያ የትዊተርን ገጽታ የያዘና ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጥ ነው
አዲሱ የሜታ መተግበሪያ በርካታ አገልግሎቶቹን በክፍያ እንዲሆኑ እየጠየቀ ያለውን ትዊተር ይፈታተናል ተብሏል
የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ የኤለን መስኩን ትዊተር የሚፎካከር አዲስ መተግበሪያውን ከነገ በስቲያ ሀሙስ በይፋ ስራ ያስጀምራል።
“ትሪድስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው መተግበሪያ በጽሁፍ ሃሳብ መለዋወጫ መድረክ እንደሚሆንና ከኢንስታግራም ጋር እንደሚቆራኝ ሜታ ገልጿል።
አፕ ስቶር ላይ የተለቀቀው የ“ትሪድስ” ገጽታ ከትዊተር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።
በርግጥ ማርክ ዙከርበርግ የሌሎች ተፎካካሪ ኩባንያዎችን የፈጠራ ሃሳብ በመውሰድ ሲታማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜው አይደለም።
የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ (ሪልስ)ን ከቲክቶክ፤ ለ24 ስአት የሚቆዩ ምስሎች (ስቶሪስ)ን ደግሞ ከስናፕቻት የኮረጀው ዙከርበርግ አሁን ደግሞ “ትሪድስ”ን ከትዊተር ወስዶ ስራ ሊያስጀምር ነው ተብሏል።
ሜታ ትዊተርን የሚገዳደር መተግበሪያ እየሰራ መሆኑ በተገለጸ ማግስት ኤለን መስክ “አለም ያለአማራጭ ሁለመናዋ በዙከርበርግ ፌስቡክ መዳፍ ውስጥ መውደቁን በቃኝ የምትልበት ጊዜ ተቃርቧል” የሚል አስተያየትን መስጠቱ ይታወሳል።
ለዚህ ትዊት ከአንድ ተጠቃሚ የተሰጠው ምላሽም ኤለን መስክ እና ማርክ ዙከርበርግን በቡጢ ፍልሚያ ይለይልን እስከማስባል ማድረሱ አይዘነጋም።
ሜታ “ትሪድስ”ን ሊለቅ እንደሆነ በሚገልጸው ዜና ስርም መስክ የሜታን ኢፍትሃዊ አካሄድ የሚቃወም አስተያየቱን መስጠቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ትዊተር ባለፈው ቅዳሜ ተጠቃሚዎች የሚመለከቱት የትዊት መጠንን መገደቡን ማሳወቁ ይታወሳል።
ከዚህም ባሻገር ትዊትዴክ የተሰኘውን መልዕክት መለጠፊያ ወይም ዳሽቦርድ በ30 ቀናት ውስጥ ወደ ክፍያ ስርአት ሊያስገባ መሆኑን ነው የገለጸው።
ኩባንያው በአለማችን ቱጃር በ44 ቢሊየን ዶላር ከተገዛ በኋላ ገቢውን ያሳድጋሉ የተባሉ ማሻሻያዎች እያደረገ ነው።
ሜታ የፊታችን ሀሙስ በይፋ ወደ ስራ አስገባዋለው ያለው መተግበሪያ (ትሪድስ) ግን ምንም አይነት ገደብ የሌለበትና በነጻ የሚቀርብ ነው ተብሏል።
ይህም አገልግሎቶቹን እየገደበ ያለውን ትዊተር ደንበኞች ለማስኮብለል ሊረዳው እንደሚችል ተገምቷል።
የዶናልድ ትራምፕን “ትሩዝ ሶሻል” እና ማስዶንን ጨምሮ በርካታ ትዊተርን የመሰሉ መተግበሪያዎች ቢተዋወቁም በሚፈለገው መጠን የመስክን ኩባንያ ሊገዳደሩት አልቻሉም።