አሜሪካ እና ኔቶ ሩሲያን ለማጥፋት በዩክሬን የጦር ሜዳ ላይ ድልን መቀዳጀት ይፈልጋሉ- ሰርጌ ላቭሮቭ
ከፍተኛ ዲፕሎማቱ፤ ጦርነቱን የማቆሚያ ቁልፍ ያለው በኪቭ እና ዋሽንግተን እጅ ነው ሲሉ ተናግረዋል
ላቭሮቭ፡ አሜሪካ በዩክሬን ጦርነት “ዋነኛ ተጠቃሚ” ሆና በኢኮኖሚ እና በወታደራዊ ትርፍ እያገኘች ነው ብለዋል
አሜሪካ እና ኔቶ ሩሲያን ለማጥፋት በዩክሬን ጦር ሜዳ ድል እየፈለጉ ነው ሲሉ የሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተናገሩ፡፡
ላቭሮቭ በሩሲያ መንግስት ከሚመራው ታስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ " የምእራቡ ዓለም ሀገራት እና በእነሱ ቁጥጥር ስር የሚሽከረከሩት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ ድርጊቶች የዩክሬን ቀውስ ዓለም አቀፋዊ ገጽታን የሚረጋግጡ ናቸው" ብለዋል፡፡
"የአሜሪካ እና የኔቶ አጋሮቿ ስትራቴጂካዊ ግብ ሩሲያን በጦር ሜዳ ድል በማድረግ ሀገራችንን በከፍተኛ ሁኔታ ለማዳከም አልፎ ተርፎም ለማጥፋት የሚያስችል ዘዴ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም" ሲሉም ተደምጠዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
አሜሪካ በዩክሬን ጦርነት “ዋነኛ ተጠቃሚ” ሆና በኢኮኖሚ እና በወታደራዊ ትርፍ እያገኘች እንዳለች የተናገሩት ላቭሮቭ፥ “አውሮፓን የበለጠ ለመገዛት እንዲያስችላት ባህላዊውን የሩሲያ እና አውሮፓን ግንኙነት የማፍረስ ጂኦፖለቲካዊ ግብ አድርጋ እየሰራች ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ፔንታጎን ወታደራዊ ግጭቶችን ከፍ በማድረግ ለመጪዎቹ አመታት የጦር መሳሪያ ለማቅረብና ለመሸጥ የሚያስችለውን እቅድ ነድፎ ለአሜሪካ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ትዕዛዞችን ማስተላለፉም ነው የገለጹት፡፡
ላቭሮቭ የአሜሪካ ፖለቲከኞች በአንድ በኩል በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሚደረገውን ማንኛውንም አይነት ግጭት በይፋ እየተቃወሙ በሌላ በኩል “ በማጭበርበር” ኬቭን ወደ ኔቶ ለማስገባት እየሞከሩ ነው ሲሉም ከሰዋል።
“ይህ ንጹህ ግብዝነት ነው፤ የሕብረቱ አባል ሀገራት ከዩክሬን ጎን ተሰልፈው የግጭቱ አካል ሆነዋል” ሲሉም ተናግረዋል ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ላቭሮቭ፡፡
ኬቭ በምዕራቡ ዓለም እና በሩሲያ መካከል “ ግጭት” እንዲፈጠር የበኩሏን ሚና እየተጫወተች ነው ሲሉም ላቭሮቭ ከሰዋል፤ ባለፈው ወር በፖላንድ የታየውን የሚሳኤል ክስተት ለአብነት በመጥቀስ፡፡
ለዩክሬን ጦርነት መባባስ የምእራቡ ዓለምን ተጠያቂ የምትታደርገው ሩሲያ፤ አሁንም ጦርነት ለማቆም ዝግጁ መሆኗ ገልጻለች፡፡
እንደ ላቭሮቭ ከሆነ ጦርነቱን የማቆሚያ ቁልፍ ያለው በኬቭ እና ዋሽንግተን እጅ ነው፡፡
ሀገራቱ ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም አስባለች በማለት ውሸት ከማዛት ተቆጥበው፤ የሞስኮ ስጋቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሄ ማምጣት እንደሚችሉም ነው ላቭሮቭ የተናገሩት፡፡