ቢሊየነሮቹ የቡጢ ፍልሚያቸውን በሎስ አንጀለስ ለማድረግ አስበዋል
የአለማችን ቀዳሚው ቱጃር ኤለን መስክ እና የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ በሪንግ ውስጥ በቡጢ ሊፈታተሹ ነው ተብሏል።
መስክ ባለፈው ማክሰኞ ፌስቡክ ትዊተርን የሚገዳደር መተግበሪያን እያበለጸገ ነው በሚለው ዜና ስር የሰጠው አስተያየት የነገሩ ሁሉ ጅማሮ ነበር።
የትዊተር፣ ቴስላ እና ስፔስኤክስ መስራችና ባለቤቱ “አለም ያለአማራጭ ሁለመናዋ በዙከርበርግ ፌስቡክ መዳፍ ውስጥ መውደቁን በቃኝ የምትልበት ጊዜ ተቃርቧል” የሚል አስተያየትን ሰጥቷል።
ለዚህ አስተያየትም አንድ የትዊተር ተጠቃሚ ምላሽ ይሰጣል፤ “መስክ ልትጠነቀቅ ይገባል፤ ዙከርበርግ ጂዩ ጂትሱ (የማርሻል አርት) ሰልጥኗል” የሚል።
መስክም ለዚህ አስተያየት “ልፋለመው ዝግጁ ነኝ” የሚል ምላሽን ይስጣል።
የፌስቡክ መስራቹ እና የአለማችን 10ኛው ቢሊየነር ማርክ ዙከርበርግም በኢንስታግራም ገጹ ላይ የመስክን ትዊት አያይዞ የት እንደምንጋጠም ቦታውን አሳውቀኝ የሚል መልዕክቱን ይለጥፋል።
የትዊተር ተጠቃሚዎችም ይህን የዙከርበርግ የኢንስታግራም መልዕክት ትዊተር ላይ ሲያጋሩት፥ መስክ “እውነት ከሆነ አደርገዋለሁ፤ ላስ ቬጋስ ኦክታጎን እንገናኝ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
52ኛ አመቱን በዚህ ወር የሚይዘው ኤለን መስክ እና የ39 አመቱ ዙከርበርግ በርግጥስ በሪንግ ውስጥ ገብተው በቡጢ ይናረቱ ይሆን? የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
የአለማችን አንደኛው ቱጃር የማህበራዊ ሚዲያ ተቀናቃኙን እንዴት እንደሚዘርረው በቀልድ መልክ የሚሰነዝራቸውን አስተያይቶች ማጋራቱን ገፍቶበታል፤ ዙከርበርግ ግን ሙያ በልብ ነው ያለ ይመስላል፤ የሚጋጠሙበትን ቦታ ብቻ ጠይቆ ዝምታን መርጧል።
የሁለቱ ቢሊየነሮች ፍልሚያ እውን ይሆን ዘንድ በርካቶች ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው ብሏል ዘ ቨርጅ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ድረገጽ።
ግጥሚያቸው ምን ሊመስል እንደሚችል የሚያሳዩ አዝናኝ ሚሞችም ትዊተር፣ ፌስቡክና ኢንስታግራምን አጥለቅልቀውታል።