“በተሰራው ስህተት ገንዘባችን ተበላ” የሚል ከፍተኛ ቅሬታ ድጋፍ ሲያደርግ ከነበረው ህዝብ ሲቀርብ ነበረ
“ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚችለውን እያደረገ ቢሆንም ሜቴክ ግን ሕዝቡ በእኛ ላይ ያለውን እምነት አሳጥቶናል”
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በገንዘብ ለመደገፍ በርካታ አማራጮች ተዘርግተዋል፡፡ የቦንድ ሽያጭ እና የ8100 A የአጭር መልዕክት የድጋፍ ማሰባሰቢያ መንገዶችም ከነዚህ አማራጮች መካከል ናቸው፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ወርሃ ሰኔ 2012 ዓ/ም ድረስም ከሃገር ውስጥ የቦንድ ሽያጭ እና ከልገሳ ከ12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል እንደ ግንባታው ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት መረጃ፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጽሕፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም እንደገለጹት ከዳያስፖራ የቦንድ ሽያጭና ልገሳ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሲገኝ ከልዩ ልዩ ገቢዎች ደግሞ ከ244 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡
እስካሁን በነበረው የገቢ አሰባሰብ ሂደት በጥቅሉ 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገደማ ገንዘብ እንደተሰበሰበም ነው አቶ ኃይሉ የተናገሩት፡፡
ግንባታውን በዐቅማቸው ለመደገፍ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሁሉ ሲገለገሉበት የነበረው የ8100 A የሞባይል የአጭር መልዕክት ገቢ የማሰባሰቢያ ዘዴ ይህን ገቢ በማሰባሰብ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦን አበርክቷል፡፡
ሁሉም የዐቅሙን በቀላሉ እንዲያበረክት በማስቻል ረገድም የማይናቅ ድርሻ ነበረው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የግንባታው ደጋፊዎችም በዚሁ ዘዴ የድጋፍ እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡
በተጀመረበት አመት 80 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ያስቻለው አማራጩ በ2008 ዓ.ም ደግሞ 48 ሚሊዮን ብር አስገኝቷል፡፡
“ሜቴክ ሕዝቡ በእኛ ላይ ያለውን እምነት አሳጥቶናል”
አቶ ኃይሉ ሕብረተሰቡ ግንባታውን ለመደገፍ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የተጀመረው ስራ ከፍተኛ ፈተና ገጥሞት እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ይህም የግድቡን የኤሌክትሮ መካኒካልና የሃይድሮ ስቲል ስትራክቸር ሥራ ለመስራት ኃላፊነቱን ተረክኖ የነበረው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) ኃላፊነቱን በወጉ ካለመወጣቱ እና መስራት የነበረበትን ስራ በወቅቱ በተገቢው መንገድ ባለማጠናቀቁ ነው፡፡ በዚህም ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል፡፡
“በተሰራው ስህተት ገንዘባችን ተበላ” የሚል ከፍተኛ ቅሬታ ድጋፍ ሲያደርግ ከነበረው የህብረተሰብ ክፍል ሲቀርብ እንደነበርም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
“በጽ/ቤቱ የምንሰራ ሰዎች ጋር እየደወሉም ጭምር ‘ገንዘባችንን አከሰራችሁት፣ ጠላቶቻችን እናንተ ናችሁ’” የሚሉ ዛቻዎች ይደርሷቸው እንደነበርም ያስቀምጣሉ ምንም እንኳን ጽህፈት ቤቱ የሚሰበሰበውን ገንዘብ በቀጥታ ወደ ፕሮጀክቱ ገቢ የሚደረግ ቢሆንም፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገው የአመራር ለውጥ ግን በግድቡ ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታትና የሕዝብን አመኔታ ለመመለስ አግዟል እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም መንግስት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ተደጋግመው የሚሰሙ የ‘ለግድቡ የተዋጣው ገንዘብ ተበልቷል፣ ለታቀደው ነገር አልዋለም’ መሰል አስተያየቶችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ተጠያቂነት የማስፈን ስራዎች መጀመራቸውንም የተናገሩት፡፡
ቀደም ሲል በተጠቀሱት ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረው የሕዝብ ተሳትፎ አሁን ላይ ተመልሶ እየተነቃቃ መሆኑን ያነሱት አቶ ኃይሉ በተጠናቀቀው ወርሃ ሰኔ 2012 ዓ/ም ብቻ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡