ግድቡን የተመለከቱ ቀጣይ የቤት ስራዎች ምንድናቸው?
የግድቡን ከፍታ 590 ሜትር በማድረስ ተጨማሪ 13 ነጥብ 4 ቢኩሜ ውሃ ለመያዝ የሚያስችሉ ስራዎችም ይሰራሉ
በ2014 ዓ/ም ኃይል ማንጨት የሚጀምሩ 11 ተርባይኖች ተከላ በቀጣዩ አመት ይካሄዳል
በ2014 ዓ/ም ኃይል ማንጨት የሚጀምሩ 11 ተርባይኖች ተከላ በቀጣዩ አመት ይካሄዳል
የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩን ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢንጂነር) የህዳሴውን ግድብ አጠቃላይ የድርድር ሂደቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው ዌቢናር (የኦንላይን ቨርቹዋል ውይይት) ለተሳተፉ አምባሳደሮች ሰፊ ማብራሪያን ሰጥተዋል፡፡
ግድቡ ለኢትዮጵያና ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ስለሚኖረው ጥቅም ለውይይቱ ተሳሳታፊዎች ያስረዱት ሚኒስትሩ ቀጣይ ተግባራትን በተመለከተም አብራርተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከሆነ በቀጣይ ዓመት ኃይል እንደሚያመነጩ የሚሞከሩትን “ሁለት ተርባይኖች ውሃ ማስተላለፊያ ‘ፔንሰቶኮች’ እና የ‘ቦተም አውትሌት’ እንዲሁም የሁለቱን ተርባይኖችና የኤሌክትሪክ ስራ ማጠናቀቅ” ይጠበቃል፡፡
ውሃው ሳይቋረጥ እንዲያልፍ፣ የግድቡ ከፍታ ወደ 590 ሜትር እንዲያድግ፣ ተጨማሪ 13 ነጥብ 4 ቢኩሜ ውሃ ከመያዝ ባለፈ በ2014 ዓ/ም ኃይል ማንጨት የሚጀምሩ 11 ተርባይኖች ተከላ እንደሚካሄድም ነው ያስረዱት፡፡
በ2015 ዓ/ም የግድቡ ከፍታ ከ590 ሜትር ወደ 645 ሜትር እንዲደርስና ግንባታው እንዲጠናቀቅ፣ መያዝ ያለበትን ውሃ በ‘ሪዘርቯዬር’ እንዲይዝ እና ኃይል ማመንጨቱን እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡
በ2016 ዓ/ም ግድቡ ያልሞላ ከሆነ ተጨማሪ ውሃ በመያዝ ኃይል የማመንጨቱ ስራ ይቀጥላል፤ ከግድቡ ጋር የተያያዙ ተጓዳኝ ስራዎች ይሰራሉም፡፡
ሃገራቱ ስምምነት ባልተደረሱባቸው የቴክኒክ ስራዎች እና ስምምነት ባልተደረሰባቸው የስምምነት ጉዳዮችና የህግ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት በማድረግም መስራትም ከድርድሩ ጋር የተያያዙ ቀጣይ የቤት ስራዎች ናቸው፡፡
ዌቢናሩን በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ (ዶ/ር) የመሩት ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው እና ሌሎች በተለያዩ ሃገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ በእስካሁኑ የድርድር ሂደቶች የተሳተፉ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡