“ከአሜሪካ በኩል ድጋፍ ይቋረጣል የሚል ይፋዊ ነገር አልደረሰንም” ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
መንግስት በኮሮና ምክንያት ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን እያገዘ መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል
የሕዳሴው ግድብ የውኃ ሙሌት የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም ለዓለም ያሳወቀ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለጸ
“ከአሜሪካ በኩል ድጋፍ ይቋረጣል የሚል ይፋዊ ነገር አልደረሰንም” ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለኢትዮጵያ የሚደረጉ ድጋፎችን ያዝ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ከሰሞኑ ሲዘገብ ነበር፡፡
ፎሬይን ፖሊሲ በተባለ መጽሔት ላይ በወጣው ጽሁፍ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን ድጋፍ ታጤናለች ስለመባሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ የደረሰ ይፋዊ መረጃ አለመኖሩን አስታውቋል፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳች ዙሪያ ዛሬ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውኃ ሙሌትን በተመለከተ ከሰሞኑ “አሜሪካ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ላትሰጥ እንደምትችል እየተገለጸ ነው” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ከአሜሪካ በኩል የድጋፍ እርዳታ ይቋረጣል የሚል ይፋዊ መረጃ እንደሌለ ገልጸው ፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት መልካም ግንኙነት እንዲቀጥል እንደምትፈልግ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት የአሜሪካ ህዝብ እንደሚረዳ ያስታወቁት አምባሳደር ዲና “ከዋሽንግተን ጋር ያለን ግንኙነታችን እንዲድበላሽ አንፈልግም ፤ የአሜሪካ ህዝብ ፍላጎት ይሄው እንደሚሆን አልጠራጠርም” ብለዋል።
ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ይደረጋል ስለተባለው ውይይት የተጠየቁት አምባሳደር ዲና ዉይይቱ የአፍሪካ ሕብረት በሚያወጣው መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ገልጸው በቅርቡ ሊሆን እንደሚችል ነው ያስታወቁት፡፡
የሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ እና ተቀባይነት እንዲኖረው ያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
አምባሳደር ዲና የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር እና የቢሮ አባላቱ የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካውያን እንዲፈታ ላደረጉት ጥረት ኢትዮጵያ ምስጋና አቅርባለች ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በውጭ ያሉ ዜጎች በፍላጎት እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው “ወደ ሀገር ቤት ከመጡ በኋላም ምቹ ሁኔታ እንዲኖር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
እስካሁን ከቤሩት 656፣ ከአቡዳቢ 72፣ ከሳዑድ አረቢያ ከ3ሺ 500 በላይ፣ ከኩዌት 1023 እንድሁም ከጎረቤት ከ 24ሺ 700 በላይ ዜጎች በድምሩ 30ሺ 87 ዜጎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን በየመን ያለው ሁኔት ግን አስቸጋሪ ነው” ብለዋል፡፡