በመተከል ዞን ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ
የሰዓት እላፊ ገደቡን ተላልፎ የሚገኝ እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል
በዞኑ በዜጎች ላይ ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ በርካቶች መደምሰሳቸውን ግብረ ኃይሉ ገልጿል
በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደው እርምጃ በርካቶች መደምሰሳቸውን በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል አባል ብርጋዴር ጄነራል አለማየሁ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለጹት በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደው እርምጃ በርካቶች ሲደመሰሱ ከፊሎቹ ተማርከዋል።
ያመለጡ የታጣቂ ቡድኑን አባላት የማደን ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በመተከል ዞን የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን በማደን “በ17 ቀበሌዎች የሚገኙ ሽፍቶችን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ” እንደተቻለም አስታውሰዋል።
ከሁለት ቀን በፊት በዞኑ “የኦነግ ሸኔና የሕወሓት ተላላኪ ታጣቂ ቡድን አባላት በፈጸሙት ጥቃት የ74 ንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን” ብርጋዴር ጄነራል አለማየሁ ገልጸዋል።
ግብረ ኃይሉ የታጣቂውን የሽፍታ ቡድን እንቅስቃሴ በመከታተል የተቀናጀ የሕግ ማስከበር እርምጃ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት ግብረ ኃይሉ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጾ ፤ ይህንን እኩይ ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ብርጋዴል ጄነራል አለማየሁ እንዳሉት ከትናንት ጀምሮ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል።
በዚህም ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ በአካባቢው ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አይፈቀድም።
ይህንን ገደብ ተላልፎ የሚገኝ እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ ካለ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ ታውቋል።