ሜታኖልን ወደ ዘላቂ የአውሮፕላን ነዳጅ በመቀየር የተደረገው የተሳካ ጉዞ
ማስዳር ከቶታል ኢነርጂ እና ኤርባስ ጋር በመተባበር ያደረጉት ሙከራ ለአቪየሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ ስኬት ነው ተብሏል
የኤምሬትስ ሄሊኮፕተር በቅርቡ በ”ዘላቂ ነዳጅ” የተሳካ ጉዞ ማድረጓ ይታወሳል
ሜታኖልን ወደ “ዘላቂ ነዳጅ” በመቀየር የተሳካ የአውሮፕላን በረራ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።
በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው የሙከራ ጉዞው የተደረገው።
የኤምሬትስ የኢነርጂ ኩባንያ ማስዳር ከቶታል ኢነርጂ፣ ከኤርባስ፣ ከፋልኮን የአቪየሽን ኩባንያ እና አክሰን የቴክኖሎጂ ፈቃድ ሰጪ ኩባንያ በመተባበር በዱባይ ስኬታማውን ሙከራ አድርገዋል።
ሜታኖልን ከብክለት ወደ ጸዳው የአውሮፕላን ነዳጅ (“ዘላቂ ነዳጅ”) ለውጦ መጠቀም በፈረንጆቹ 2016 ህጋዊ ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል።
በዱባይ የተደረገው የተሳካ በረራም ሚታኖል የቀጣዩ የአቪየሽን ነዳጅ አማራጭ እንደሚሆን ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑ ነው የተገለጸው።
“ዘላቂ ነዳጅ” የአቪየሽን ኢንዱስትሪው በከባቢ አየር ብክለት ያለውን ድርሻ በእጅጉ እንደሚቀንስ ታምኖበታል።
አሁን ላይ ጥቅም ላይ እየዋለ ከሚገኘው የአውሮፕላን ነዳጅ የሚለቀቅ በካይ ጋዝን በ80 በመቶ እንደሚቀንም ነው የማስዳር መረጃ የሚያሳየው።
የኤምሬትስ ሄሊኮፕተር በቅርቡ በ”ዘላቂ ነዳጅ” የተሳካ ጉዞ ማድረጓ ይታወሳል።
በባህረሰላጤውም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ የመጀመሪያ የሆነው ጉዞ ኤምሬትስ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው የአየር ብክለት እንዳያስከትል እያደረገች ያለውን ጥረት ያሳያል መባሉ አይዘነጋም።
ዘጠነኛ ቀኑን የያዘው ኮፕ28 የአየር ትራንስፖርት በከባቢ አየር ብክለት ያለው ድርሻ በሚቀንስባቸው መንገዶች ላይ በስፋት እየተመከረበት ነው።