አሜሪካ “ህገወጥ የእንቁላል ዝውውር” አሳስቦኛል አለች
ከወደ ሜክሲኮ በርካታ ሰዎች በህገወጥ መንገድ እንቁላል ይዘው ሊሻገሩ ሲሉ መያዛቸውን የድንበር ተቆጣጣሪዎች ተናግረዋል
በአሜሪካ የእንቁላል ዋጋ በ60 በመቶ መጨመሩ ተነግሯል
አሜሪካ ህገወጥ የሰዎች ብቻ ሳይሆን የእንቁላል ዝውውር እንዳሳሰባት ገለጸች።
በሀገሪቱ የእንቁላል ዋጋ በታህሳስ 2022 ካለፈው አመት የ60 በመቶ ጭማሪ አስተናግዷል። ይህም የእንቁላል ዋጋ ረከስ ከሚልባት ሜክሲኮ በህገወጥ መንገድ እንዲገባ ማድረጉ ነው የተነገረው።
የሀገሪቱ የጉምሩክ እና ድንበር ተቆጣጣሪዎችም እንቁላል ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ይዘው ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
አሜሪካ በታሪኳ ከፍተኛውን ጉዳት ያስከተለ የዶሮ ጉንፋን ማስተናገዷ የእንቁላል ዋጋ እንዲያሻቅብ ማድረጉ ተነግሯል።
በሱቆች አንድ ሰው ምን ያህል እንቁላል መግዛት እንደሚችልም ገደቦች የተቀመጡባቸው አካባቢዎች አሉ።
ይህም፥ ከበድ ያለ ቅጣት ቢኖረውም ከውጭ ሀገራት እንቁላልን ይዘው ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን ነው የአሜሪካው ኤን ፒ አር ሬዲዮ የዘገበው።
በሜክሲኮ 30 እንቁላሎችን በ3 ነጥብ 40 ዶላር መግዛት ይቻላል፤ በአሜሪካ ግን 12 እንቁላሎችን ለመግዛት 7 ነጥብ 37 ዶላር ይጠየቃል።
እንደ ቴክሳስ ያሉ ግዛቶችም ጉዳዩ በህግ የተከለከለ ቢሆንም ከእጥፍ በላይ ቅናሽ ያለውን እንቁላል ከሜክሲኮ እየገዙ ነው ተብሏል።
በድንበር ላይ ፍተሻ ሲደረግ በህገወጥ መንገድ እንቁላል ለማስገባት ሲሞክሩ የተያዙ ሰዎች 300 ዶላር ይቀጣሉ።
አሜሪካ ከውጭ ሀገራት ዶሮም ሆነ እንቁላል ከውጭ ሀገር ማስገባትን በህግ መከልከሏን ዘገባው አስታውሷል።
ከሜክሲኮም የዶሮ ጉንፋንን ለመከላከል በሚል ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ ዶሮ ማስገባት መቆሙ ተገልጿል።
ስታስቲካ ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው፥ እያንዳንዱ አሜሪካዊ በአመት በአማካይ 288 እንቁላሎችን ይመገባል።