ሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ፑቱንን እንድታስር የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አደረገች
ፕሬዝዳንት ፑቲን የፊታችን ጥቅምት በተመራጯ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል
ዩክሬን ሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ፑቲንን እንድታስር ጥያቄ አቅርባ ነበር
ሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ፑቱንን እንድታስር የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አደረገች።
በሜክሲኮ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክላውዲያ ሼንቡአም ማሸነፋቸው ይታወሳል።
አዲሷ ተመራጭ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት በፈረንጆቹ ጥቅምት አንድ ቀን ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል።
በርካታ ሀገራት በፕሬዝዳንቷ በዓለ ሲመት ላይ እንዲገኙ ግብዣ የቀረበላቸው ሲሆን ፕሬዝዳንት ፑቱን ግብዣው ከቀረበላቸው መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ሩሲያ ከሜክሲኮ የቀረበላትን ግብዣ እንደተቀበለች መገለጹን ተከትሎ ዩክሬን ፕሬዝዳንት ፑቲን ወደ ሜክሲኮ እንደገቡ እንዲታሰሩ ጥያቄ አቅርባለች።
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽመዋል በሚል የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱ አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎም ሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ፑቲንን አስራ ለጦር ወንጀል ፍርድ ቤት እንድትሰጥ በዩክሬን በኩል ጥያቄ ቀርቦላታል።
ተሰናባቹ የሜክሲኮ ፕሬዚዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ የዩክሬንን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ "ጉዳዩ እኛን አይመለከትም" ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሜክሲኮ የዓለም አቀፉ ጦር ወንጀል ፍርድ ቤት አባል ስትሆን ሩሲያ በአንጻሩ አባል አይደለችም።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ክላውዲያ ሼንቡአም የሜክሲኮ አዲስ ፕሬዝዳንት ሆና ስትመረጥ የእንኳን ደስ አለሽ መልዕክት ካስተላለፉ የዓለም መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በወቅቱ ሩሲያ በደቡብ አሜሪካ ካሏት ወደጅ ሀገራት መካከል ሜክሲኮ ዋነኛዋ ናት ብለው ነበር።