የአውሮፓ ህብረት ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች ውስጥ 1.6 ቢሊየን ዶላር ለዩክሬን አስተላለፈ
ምእራባውያን ሀገራት 300 ቢሊየን ዶላር የሩሰያ ሀብት አግደው ይዘዋል
ሩሲያ ንብረቶቿን አሳልፎ መስጠት ሌላ መዘዝ ያስከትላል በማለት ማስጠንቀቋ ይታወሳል
የአውሮፓ ህብረት ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዳላር ለዩክሬን ማስተላለፉን አስታወቀ።
ህብረቱ በዛሬው እለት በመጀመሪያ ዙር ለዩክሬን ያስተላለፈው ገንዘብ ከታገደው የሩሲያ ንብረት ላይ የተገኘ የወለድ ትርፍ መሆኑም ተነግሯል።
27 የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ባደረጉት ስብሰባ ከተያዘው 225 ቢሊየን ዶላር የሩሲያ ገንዘብ ላይ የሚገኘውን የወለድ ትርፍ ዩክሬን ጦሯን እንድታተጠናክርበት እና በጦርነት የደረውሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት እንድታውል ለመስጠት መስማማታቸው ይታወሳል።
አብዛኛው የተያዘው የሩሲያ ገንዘብ ቤልጂየም ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ከተትሎ በተጣለ ማዕቀብ ነው ገንዘቡ የታገደው።
ቤልጂየም የታገደው የሩሲያ ገንዘብ በየዓመቱ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ የወለድ ትርፍ እንዳለው አስታውቃለች።
ከዩክሬን ጎን ነኝ ያለው የአውሮፓ ህብረት ከተያዘው የሩሲያ ገንዘብ ከተገኘ የወለድ ትርፍ ውስጥ 1.6 ቢሊየን ዶላር ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እና መከላከያ ኃይል ጥቅም ላይ እንዲውል መወሰኑን አስታውቋል።
ሩሲያ ከዚ ቀደም በሰጠችው መግለጫ፤ እንዳይንቀሳቀሱ እገድ የተላለፈባቸው የሩሲያዊያን ሀብትን ለዩክሬን መስጠት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ህግ እንደሌለ መግለጿ ይታወሳል።
ድርጊቱ ሌላ ዓለም አቀፍ መዘዝ ያስከትላል ስትል በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃም ነበር።