ፕሬዝዳንት ፑቲን ተደራድረው ያስለቀቁት የእድሜ ልክ እስረኛ ቫዲም ክራሲኮቭ ማን ነው?
ቫዲም ክራሲኮቭ በጀርመን ሀገር በሰው ግድያ ወንጀል የእድሜ ልክ እስረኛ ነበር

ግለሰቡ የሩሲያ ጠላት ነው የተባለን ሰው እንዲገድል በስደተኞች ስም ወደ ጀርመን እንዲጓዝ የተደረገ ነበር
ፕሬዝዳንት ፑቲን ተደራድረው ያስለቀቁት የእድሜ ልክ እስረኛ ቫዲም ክራሲኮቭ ማን ነው?
ከሰሞኑ የዓለማችን ቁንጮ የሚባሉ ሀገራት 24 ተጽዕኖ ፈጣሪ የተባሊ እስረኞችን ተለዋውጠዋል፡፡
የእስረኛ ልውውጥ የሚል ስም የተሰጠው ይህ ክስተት ታሳሪዎቹ ባለፉት ዓመታት ከተደረጉ የዓለማችን አንኳር ክስተቶች መካከል ዋነኛ ተዋናዮች የነበሩ ናቸው፡፡
የእስረኛ ልውውጥ ያደረጉት አሜሪካ እና ሩሲያ ናቸው የተባለ ቢሆንም እስረኞቹ ግን በአውሮፓ ሀገራትም ታስረው የነበሩ ናቸው፡፡
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተደረገ ከባድ የእስረኞች ልውውጥ ነው በተባለው በዚህ ልውውጥ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተደራድረው ካስፈቷቸው እስረኞች መካከል ቫዲም ክራሲኮቭ አንዱ ነው፡፡
ክራሲኮቭ በስደተኞች ስም ወደ ጀርመን የገባ ሩሲያዊ ሲሆን በፈረንጆቹ 2019 ላይ አንድ ሰው ግድሎ የእድሜ ልክ እስረኛ ነበር፡፡
ይህ ሰው በወቅቱ ማንነቱን የቀየረ አለባበስ በመጠቀም በድምጽ አልባ ሽጉጥ ዘሊምካን ካንጎሽቪሊ የተሰኘን ሰው በበርሊን ዋና ጎዳናዎች ላይ ገድሏል ተብሏል፡፡
ግድያው ከተፈጸመ በኋላ በወጣ መረጃ መሰረት ዘሊምካን የተሰኘው ሰው በዜግነቱ ጆርጂያዊ ሲሆን የቺቺኒያ አማጺ ቡድን ኮማንደር በመሆን አገልግሏል፡፡
የሩሲያ ጦርን ሲዋጋ የነበረው የቺቺኒያ አማጺ ቡድን መሪ የነበረው ይህ ሰው ወደ ጀርመን ገብቶ ተጠልሎ ሲኖር እንደነበር ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመሬት ናዳ ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ሀዘናቸውን ገለጹ
በተመሳሳይ መንገድ በስደተኞች ስም ወደ ጀርመን የገባው ሩሲያዊው ቫዲም ክራሲኮቭ ይህን የቀድሞ የቺቺኒያ አማጺ ቡድን ኮማንደርን ተከታትሎ እንዲገድል ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡
ክራሲኮቭ የተሰጠውን ተልዕኮ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ላይ በተለይም ጥብቅ ጥበቃ ከሚደረግበት የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አጠገብ ግድያውን ፈጽሞ ሊያመልጥ ሲል ተይዟል፡፡
የጀርመን ፍርድ ቤትም ግድያውን በፈጸመው ቫዲም ክራሲኮቭ ላይ የእድሜ ልክ እስራት የፈረደበት ሲሆን ግለሰቡ የእስር ጊዜውን እየፈጸመ ነበር፡፡
ሩሲያ ይህ ሰው ከእስር እንዲለቀቅ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ የቆየች ሲሆን ከዚህ በፊት በሩሲያ ታስራ የነበረችው አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ስፖርተኛ ብሪትኒ ግሪነር ከእስር እንድትለቀቅ ሲጠየቅ በምትኩ በበርሊን የታሰረው ቫዲም ክራሲኮቭ እንዲለቀቅ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡
እንዲሁም የሩሲያ ዋነኛ ተቃዋሚ የሆነው ናቫልኒ ከእስር እንዲለቀቅ በአሜሪካ ጥያቄ ሲቀርብ በምትኩ ይህ ሰው በተመሳሳይ ከእስር እንዲለቀቅ ከስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም ናቫልኒ በድንገት በእስር ቤት እያሉ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ድርድሩ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በመጨረሻም አሜሪካ እና ሩሲያ በሶስተኛ ወገን ባደረጓቸው ድርድሮች አማካኝነት ቫዲም ክራሲኮቭን ጨምሮ 24 ቁልፍ የሚባሉ ታሳሪዎች ከእስር ተለቀዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ኤርፖርቶች ተገኝተው ነጻ የወጡ እስረኞችን አቀባበል ደረጉ ሲሆን ፕሬዝዳንት ፑቲን ቫዲም ክራሲኮቭን በአካል ሄደው ተቀብለውታል፡፡
ስደተኛ መስሎ በሸንገን ቪዛ አማካኝነት በፈረንሳይ በኩል ወደ ጀርመን እንዲገባ የተደረገው ቫዲም ክራሲኮቭ በመጨረሻም የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቀድሞ ጠባቂ እንደነበር ዶቸቪሌ ዘግቧል፡፡