የቫይረሱን ቀላል ምልክት ያሳዩት ፕሬዝዳንቱ ብሔራዊ ስራዎችን በቤተ መንግስት ሆነው እንደሚመሩ ገልጸዋል
የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ምርመራ አድርገው ቫይረሱ እንዳለባቸው ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ቀላል ምልክት እያሳዩ መሆናቸውን ገልጸው እንደማገግም “ብሩህ ተስፋ አለኝ”ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከሜክሲኮ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ሆነው ሁሉንም ብሔራዊ ስራዎች እንደሚያከናውኑ ያስታወቁ ሲሆን ከቭላድሚር ፑቲን ጋር በኮሮና ክትባት ዙሪያ የሚያተኩር ውይይት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡
የሜክሲኮ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ኦልጋ ሳንቼዝ እርሳቸውን ወክለው የዕለት ሥራዎችን የማሳወቅ ስራውን እንደሚያከናውኑም ነው ሲኤንኤን የዘገበው፡፡ በሜክሲኮ ከ 149 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ለህልፈት ሲዳረጉ ከ1 ሚሊዮን 752 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሏል፡፡